ዛሬ ደግሞ ስቶክ ማርኬትን በቀላሉ ለመረዳት ያስችለን ዘንድ የሪል ስቴት ኢንቨስትመንትን እንመለከታለን። ምክንያቱም አብዛኞቻችን ሪልስቴትን ስለምናውቀው ነው። ሪልስቴት ሲባል ቤት ወይም ህንፃ ሰርቶ አሊያም ገዝቶ መሸጥ እንዲሁም መሬት ገዝቶ መሸጥ ነው። በአገራችን ደግሞ በጣም የተለመደው መሬትን ገዝቶ መሸጥ ነው። በዚህም በርካቶች ሃብታም መሆን ችለዋል። ስለዚህ ሪልስቴት አንደኛው የሃብት መገንቢያ ኢንቨስትመንት ነው ማለት ነው። ሪልስቴት ከስቶክ ማርኬት ጋር ተቀራራቢ የሆነ ባህሪ ወይም መገለጫ አለው። ከእነዚህ አንዱ ሁለቱም የኢንቨስትመንት መሳሪያ መሆናቸው፤ ሁለቱም ሰዎች ገንዘባቸውን ኢንቨስት አድርገው ከሆነ ጊዜ በኋላ ትርፍ የሚያገኙባቸው የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ናቸው። ስለዚህ ሪልስቴትን መረዳት ስቶክ ማርኬትን በቀላሉ ለመረዳት ያግዘናልናል ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በሁለት ሚሊዮን ብር ቤት ገዛ ብለን እናስብ። ይህ ሰው ቤቱን የገዛው ለመኖሪያነት ሳይሆን ለኢንቨስትመንት ፈልግት ነው። ስለዚህ ይህ ግለሰብ ሁለት ሚሊዮን ብር በቤቱ ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ ተጨማሪ ሃብት እንዲያመጣለት በማሰብ ነው። ይህ ከሆነ እንዴት ነው ተጨማሪ ሃብት ሊያመጣለት የሚችለው? የሚለውን ስናይ ግለሰቡ ቤቱን ሲሸጥ በሁለት መንገዶች ገቢ ያገኛል። የመጀመሪያው ይህ ግለሰብ ቤቱን ሳይሸጥ አቆይቶ ዋጋው ሲጨምር ቤቱን በገዛው በ3ኛው ዓመት ላይ ለመሸጥ አቅዷል ብለን ብናስብ፤ ስለዚህ ይህ በሁለት ሚሊዮን ብር የተገዛ ቤት 1ኛ ዓመቱ ላይ የቤቱ ዋጋ በ 300 ሺህ ብር ሊጨምር ይችላል። በዚህም የቤቱ ዋጋ በመጀመሪያው ዓመት ላይ 2.3 ሚሊዮን ብር ይሆናል ማለት ነው። በ2ኛው ዓመት ላይ ደግሞ የቤቱ ዋጋ እንዲሁ በ 300ሺህ ብር ቢጨምር ጠቅላላ ዋጋው 2.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን በ3ኛው ዓመት ላይ ደግሞ በ400 ሺህ ብር ቢጨምር የቤቱ ጠቅላላ ዋጋ ሦስት ሚሊዮን ብር ህኗል ማለት ነው። ይህ ቤት እንግዲህ በየዓመቱ በዚህ መልኩ ሲያድግ ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ ኢንቨስት ያደረገው ሁለት ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ካፒታል እያልን እንጠራዋለን። ስለዚህ ይህ ግለሰብ ቤቱን በመጀመሪያ ዓመቱ ላይ ቢሸጠው 300 ሺህ ብር ያገኛል፤ በሁለተኛው ዓመት ላይ ቢሸጠው ደግሞ 600 ሺህ ብር ያተርፋል፤ እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት ላይ ቤቱን ቢሸጠው አንድ ሚሊዮን ብር ያተርፋል ማለት ነው። ስለዚህ በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ ዋናዎቹና መሰረታዊ ነገሮች የሚባሉት ሳቢና አመቺ የሆነን ቦታ አካባቢን መርጦ መግዛት አሊያም መገንባት፤ ቤቱን ወይም መሬቱን በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት፤ የቤቶችና የመሬት ዋጋ በየጊዜው ስለሚጨምር ለረጅም ጊዜ ሳይሸጡ ይዞ መቆየትና ከፍተኛ ዋጋ ሲያወጣ ጠብቆ መሸጥ ናቸው ማለት ነው።

    ወደ ስቶክ ማርኬት ስንመጣ ደግሞ ለምሳሌ ሀሁ ኩባንያ የአክሲዮን ማህበር ነው ብለን ብናስብና እንዲሁም ደግሞ ኩባንያው እያንዳንዳቸው 1000 ብር ዋጋ ያላቸው አንድ ሚሊዮን አክሲዮኖች ቢኖሩት ከእነዚህም ውስጥ 200 አክሲዮኖችን ቢሸጥና የተለያዩ ኢንቨስተሮች እዚህ ካምፓኒ ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ ኢንቨስተሮቹ የሚገዙት የኩባንያውን የባለቤትነት ድርሻ ነው ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ኢንቨስተሮች የካምፓኒውን የባለቤትነት ድርሻ ከገዙ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር አክሲዮናቸውን ጊዜ ጠብቀውና አትርፈው መሸጥ ነው። በዚህም የተነሳ ባለአክሲዮኖቹ የባለቤትነት ድርሻቸውን በመጀመሪያው ዓመት፤ በሁለተኛው አላያም በሦስተኛው ዓመት ላይ ሊሸጡ ይችላሉ። ኢንቨስትመንት ላይ ዋናው ጉዳይ ስቶኩን ወይም በሪልስቴት ላይ ደግሞ ቤቱን ወይም መሬቱን ሳይሸጡ (ዋጋቸው እስኪጨምር ድረስ) ለተወሰኑ ዓመታቶች ይዞ የመቆየት ነገር ነው ይህም በኢንቨስትመንት ቋንቋ "holding period" በመባል ይታወቃል። በኢንቨስትመን ላይ ሌሎቹ መሰረታዊ ነገሮች በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት፤ አዋጭ የሆነ ኩባንያን መርጦ አክሲዮን መግዛት ነው። ስለዚህ ከላይ በምሳሌው ላይ እንዳስቀመጥነው የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1000 ብር ነው ብለናል። በዚህም ግለሰቡ በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ያደርጋል ማለት ነው። ይህ አንድ ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል በመባል ይጠራል።

    በአክሲዮን ገበያ ላይ ኢንቨስት ያደረገ ሰው በሁለት መንገድ ገቢ ያገኛል። የመጀመሪያው በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከትርፍ ክፍፍል (dividend income) የሚያገኘው ገቢ ሲሆን፤ ሁለተኛው የገቢ መንገድ ደግሞ ከካፒታል ዕድገት (capital gain) የሚያገኘው ነው። በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይም የተሰማራ ሰው እንዲሁ ሁለት ዓይነት ገቢዎችን የሚያገኝ ሲሆን የመጀመሪያው ከኪራይ የሚገኝ ገቢ (rental income) ነው። ሁለተኛው ገቢው ደግሞ ከሽያጭ (capital gain) የሚያገኘው ነው ማለት ነው።

    ከላይ እንዳየነው አንድ ሚሊዮን ብር አውጥቶ አክሲዮን የገዛው ግለሰብ ከአንድ አክሲዮን የሚያገኘው ገቢ መቶ ብር ነው ብለን ብናስብ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከሚደረገው የትርፍ ክፍፍል 100 ሺህ ብር ሲያገኝ፤ በሁለተኛው ዓመት ላይ ደግሞ 120 ሺህ ብር፤ በሦስተኛው ዓመት ላይ ደግሞ 150 ሺህ ብር በትርፍ ክፍፍል መልክ የሚያገኝ ይሆናል።

    የዚህ ግለሰብ ሁለተኛው ገቢው ደግሞ ከካፒታል ዕድገት (capital gain) የሚያገኘው ገቢ ነው። የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1000 ብር ነው ብለናል። ግለሰቡ የገዛው የአክሲዮን ብዛት ደግሞ 1000 ስለሆነ የግለሰቡ የኢንቨስትመንት ካፒታል 1000 × 1000 = 1,000,000.00 ብር ነው ማለት ነው። ስለዚህ ግለሰቡ አክሲዮኑን በገዛ በመጀመሪያው ዓመት መጨረሻ ላይ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1500 ብር ቢሆን በሁለተኛው ዓመት ላይ 2000 ብር፤ እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት ላይ ደግሞ 2500 ብር ሊሆን ይችላል። ይህም ማለት የግለሰቡ የኢንቨስትመንት ካፒታል በመጀመሪያው ዓመት ወደ 1.5 ሚሊዮን ብር ሲያድግ በሁለተኛው ዓመት ላይ ደግሞ ወደ 2 ሚሊዮን ብር፤ እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት ወደ 2.5 ሚሊዮን ብር አደገ ማለት ነው።  ይህንንም ተከትሎ ግለሰቡ አክሲዮኑን በመጀመሪያው ዓመት ላይ ቢሸጠው በአጠቃላይ የሚያገኘው ገቢ ከትርፍ ክፍፍል 100 ብር፤ ከካፒታል ዕድገት (capital gain) ደግሞ 500 ብር ሲያገኝ በአጠቃላይ 600 ብር ያገኛል ማለት ነው። ግለሰቡ በሁለተኛው ዓመት ላይ  አክሲዮኑን ለመሸጥ ቢፈልግ ከትርፍ ክፍፍል ከመጀመሪያው ዓመት ላይ የሚያገኘው ከትርፍ ክፍፍል ብቻ በመሆኑ በዚህም 100 ሺህ ብር ሲያገኝ፤ ከሁለተኛው ዓመት ደግሞ 120 ሺህ ብር በአጠቃላይ 220 ሺህ ብር አለው ማለት ነው። ከካፒታል ዕድገቱ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር በማግኘት በአጠቃላይ 1,220,000.00 ብር ያገኛል ማለት ነው። እንደገና ደግሞ  ኩባንያው ውጤታማ እየሆነ በመምጣቱና የአክሲዮን ዋጋው ወደ 2500 ብር ማደጉን ተከትሎ በ3ኛው ዓመት ላይ አክሲዮኑን ለመሸጥ ቢፈልግ 2500 - 1000 = 1500

1500 × 1000 =  ከካፒታል ዕድገት 1.5 ሚሊዮን ብር ሲያገኝ፤ ከትርፍ ክፍፍል  ደግሞ ከመጀመሪያውና ከሁለተኛው ዓመት 220ሺህ ብር እንዲሁም በሶስተኛው ዓመት ላይ ከሚያገኘው 100 ሺህ ብር ጋር ተደምሮ በአጠቃላይ 370 ሺህ ብር ሲያገኝ በአጠቃላይ 1,870,000.00 ያገኛል ማለት ነው። ስለዚህ የማቆያ ጊዜዎቹን ስንመለከታቸው ግለሰቡ በመጀመሪያው ዓመት 600 ሺህ ብር፤ በሁለተኛው ዓመት ደግሞ 2,220,000 ብር፤ እንዲሁም በሦስተኛው ዓመት 1,870,000 ብር አግኝቷል ማለት ነው። ስለዚህ በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራው ሰው ከኪራይና ከሽያጭ ገቢ እንደሚያገኘው ሁሉ ይህም ግለሰብ ከትርፍ ክፍፍልና ከካፒታል ዕድገት ገቢዎችን ያገኛል ማለት ነው።

   ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ስቶክ ማርኬትና የሪልስቴት ኢንቨስትመንት ያላቸውን መመሳልና ልዩነቶች ጠቅለል አድርገን ስናያቸው፦

               ተመሳይይነታቸውና ልዩነቶቻቸው

* ሁለቱም የኢንቨስትመንት መሳሪያ መሆናቸውና ሰዎች ገንዘባቸውን ኢንቨስት በማድረግና ከሆነ ጊዜ በኋላ አቆይተው በመሸጥ ትርፍ የሚያገኙባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ናቸው።

*  በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ሳቢና ለኑሮ አመቺ  የሆነ ቦታና አካባቢን መምረጥ ሲሆን በስቶክ ገበያ ላይ ደግሞ አዋጭ የሆነን ኩባንያ መምረጥ ነው።

* በሪልስቴት ኢንቨስትመንት መሬትን፣ ቤትንና ህንፃዎችን በዝቅተኛ ዋጋ መግዛትና ጊዜ ጠብቆ ዋጋቸው ሲጨምር ከፍ ባለ ዋጋ መሸጥ ሲሆን በስቶክ ማርኬት ላይ ደግሞ ስቶኮችን  በዝቅተኛ ዋጋ ገዝተንና ዋጋቸው የሚጨምርበትን ጊዜ ጠብቀን መሸጥ ነው።

* ሰዎች በስቶክ ማርኬት ላይ ኢንቨስት ሲያደርጉ ከትርፍ ክፍፍል (Divided income) እና ከካፒታል ዕድገት (capital gain) ገቢ ሲያገኙ፤ በሪልስቴት ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ ከኪራይ (rental income) እና ከሽያጭ ገቢ የሚያገኙ ይሆናል።

* በሁለቱም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የማቆያ ጊዜ (holding period) በጣም መሰረታዊ ነገር ነው።

* በሪልስቴት ላይ የምንገዛውና የምንሸጠው መሬቶችን፣ ቤቶችን፣ ህንፃዎችንና ሱቆችን ሲሆን በስቶክ ማርኬት ላይ ደግሞ የምንገዛውና የምንሸጠው የገንዘብ ሰነዶችን ማለትም ስቶኮችንና ቦንዶችን ነው ማለት ነው።

ስለዚህ ስቶክ ማርኬትን ከሪልስቴት አንፃር ስናየው ይህን ይመስላል ማለት ነው!!!


❤ ❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤