በዛሬው መሰናዷችን ደግሞ በስቶክ ማርኬት ውስጥ መሳተፍ የሚችሉት እነማን ናቸው? የሚለውንና በዚህ የግብይት ስርዓት ውስጥ ምን ምን ነገሮችን ማሟላት አለባቸው? የሚለውን ጉዳይ በስፋት የምንመለከተው ይሆናል።

ስቶክ ማርኬት የሚለው ቃል "ስቶክ" ከሚለውና "ማርኬት" ከተሰኙት ቃላቶች የተመሰረተ ነው። ስቶክ ማለት ለድርጅቶች የስቶክ ባለቤትነት ማረጋገጫነት የሚሰጥ ሰርትፊኬት ሲሆን ማርኬት ደግሞ ገዥና ሻጭን የሚያገናኝ ቦታ ወይም ሲስተም ነው። ስለዚህ ስቶክ ማርኬት ማለት በአጭር አገላለፅ የአክሲዮን ገበያ ማለት ነው። በገበያ ውስጥ ደግሞ ገዥና ሻጭ እንዲሁም ገዥውንና ሻጩን የሚያገናኝ ሲስተም (platform) መኖር መቻል አለበት ማለት ነው።

    በስቶክ ማርኬት ግብይት ውስጥ ገዥና ሻጭ እንዲሁም አሻሻጮች (stock brokers) የምንላቸው አካላት አሉ። ስለዚህ ስቶክ ማርኬት በሁለት ነገሮች ላይ የተመሰረተ ሲሆን እነዚህም ስቶክ ገዥና ስቶክ ሻጭ ናቸው። ስቶክ ሻጭ በምንልበት ጊዜ ለምሳሌ ካምፓኒዎች ስቶክ አላቸው፤ ይህንን ስቶክ ደግሞ የሚሸጡት ለግለሰቦች አሊያም ለሌሎች ካምፓኒዎች ሊሆን ይችላል። በስቶክ ማርኬት ውስጥ ደግሞ ሁለት ዓይነት ግብይቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም የመጀመሪያ ደረጃ የአክሲዮን ሽያጭ (primary market) እና ሁለተኛ ዙር የአክሲዮን ሽያጭ (secondary market) በመባል ይታወቃሉ። ለምሳሌ ግለሰቦች ስቶክ ሸጡ ሲባል ይህንን ስቶክ ከየት ነው የሚያመጡት? የሚለውን ነገር ስንመለከት ግለሰቦች ከዚህ ቀደም ከሆነ ኩባንያ፣ ድርጅት ወይም ተቋም ላይ የገዙት ስቶክ ካላቸው (primary market)፤ አመቺ ጊዜ ጠብቀውና አትርፈው ለመሸጥ ይፈልጋሉ። ይህም ማለት ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የባለቤትነት ድርሻ ለሌላ ሰው ማስተላለፍ ማለት ነው። ይህ ነው እንግዲህ ሁለተኛ ዙር የአክሲዮን ሽያጭ (secondary market) የሚባለው። ከዚህ አኳያ ስቶክ ሻጮችን በምንመለከትበት ጊዜ ሁለት ዓይነት ሻጮች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው ከአሁን ቀደም አክሲዮን የገዙ ሰዎች ይህን አክሲዮናቸው ወደ ሌላ ማስተላለፍ ወይም መሸጥ የሚፈልጉና ሁለተኛዎቹ ደግሞ ነባርና በስቶክ ማርኬት ላይ የተመዘገቡ ካምፓኒዎችና (listed companies) አሊያም ደግሞ አዳዲስ ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች እንደገና በሌላ ዙር ስቶኮቻቸውን ሊሸጡ ይችላሉ ማለት ነው። እናም ድርጅቶች ስቶካቸውን በሁለት መንገድ ይሸጣሉ። የመጀመሪያው ነገር ድርጅቶቹ መስፈርቱን አሟልተው በስቶክ ማርኬቱ ላይ ሲመዘገቡ ነው።  ይህንንም 'IPO' Initial Public Offering እንለዋለን። አንድ ድርጅት በስቶክ ማርኬት ላይ ለመመዝገብ ሟሟላት ያለበት መስፈርቶች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው ድርጅቱ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የተቋቋመ መሆን መቻል አለበት። ምክንያቱም የአክሲዮን ኩባንያዎች የአደረጃጀት ስርዓታቸው ጠንካራ በመሆኑ ደህንነታቸው የተሻለ እንደሆነ ስለሚታመን ሲሆን በሁለተኛና በዋናነት ግን የአክሲዮን ባለቤቶቹ መጠን በኮርፖሬሽን ደረጃ ገደብ የሌለው በመሆኑ ነው። በዚህ ደረጃ አንድን አክሲዮን ለማቋቋም ዝቅተኛው የሰው ብዛት 5 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ ገደብ የለውም። ይህ መሆኑ ደግሞ ለስቶክ ግብይቱ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ምክንያቱም በስቶክ ማርኬት ውስጥ መሳተፍ የፈለገ ማንኛውም ሰው መሳተፍ ስለሚያስችል ነውና። ሌሎቹን የንግድ አደረጃጀቶች ስንመለከት (sole proprietorship, private limited company...) በእነዚህ የንግድ አደረጃጀቶች አክሲዮን ለማቋቋም ዝቅተኛው የሰው ብዛት 2 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 50 ሰው ነው። በዚህም የተነሳ በስቶክ ማርኬት ውስጥ መሳተፍ አይችሉም፤ ህግ ይገድባቸዋል።

    ሌላኛውና ሁለተኛው መስፈርት ደግሞ ድርጅቱ ከአሁን ቀደም ያለውንና (ቢያንስ የሦስት ዓመት) ውጤታማነቱን የሚያሳይ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ መቻል አለበት። ይህም ድርጅቱ በገቢ ደረጃ እያደገ የሚሔድ፤ በትርፋማነቱም ጥሩና ሳቢ መሆኑን መረጋገጥ አለበት ማለት ነው።

    በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምናገኘው መስፈርት ደግሞ ድርጅቱ ካለው ሀብት አንፃር የተሻለ ትርፋማነት (return on investment) ያለው ሆኖ መገኘት አለበት። ይህም ሲባል ድርጅቱ ያለው ሀብት ከዕዳ አንፃር ምን ያህል እንደሆነ ማቅረብ መቻል አለበት ማለት ነው። አንድ ድርጅት በፋይናንስ ሪፖርቱ ውስጥ ማካተት የሚኖርበት ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ሆነው ማለት ነው። ስለዚህ ድርጅቱ በስቶክ ማርኬት ላይ ለመመዝገብ ህጋዊነቱ በተረጋገጠና ዕውቅና ባለው የሂሳብ ባለሙያ የተሰራ የፋይናንስ ሪፖርት በስቶክ ማርኬት ውስጥ ይህንን ለሚሰሩ (underwriters) ወይም ደግሞ ዋስትና ሰጪ (ባንኮች ሊሆኑ ይችላሉ) ተቋማት በማቅረብ እነሱም የድርጅቱን የፋይናንስ ጤናማነት፤ የማናጀሮቹን ወይም የ CEO'ዎቹን ባህሪና ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ስብዕና በመገምገም ይህ ድርጅት በስቶክ ማርኬት ላይ ቢመዘገብ ድርጅቱም ተጠቃሚ ይሆናል፤ በዋናነት ደግሞ ከድርጅቱ ላይ አክሲዮን ወይም ስቶክ የሚገዙ ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለው ሊያምኑበት የሚችሉትን መስፈርት ማሟላት ይጠበቅበታል ማለት ነው። ይህንን ለማረጋገጥና በድርጅቱ ላይ አስፈላጊውን ጥናት ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ምናልባትም ሒደቱ ከ3 - 6 ወር ሊፈጅ ይችላል። ይህ ሁሉ ሆኖ ድርጅቱ በስቶክ ማርኬት ላይ ለመመዝገብ ብቁ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በስቶክ ማርኬት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ይመዘገባል ማለት ነው። ይህንን ደግሞ IPO (Initial Public Offering) ወይም ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ የአክሲዮን ሽያጭ (primary market) እንለዋለን። እንዲሁም ደግሞ ይህ ድርጅት በስቶክ ማርኬት ላይ በመቅረብ ተጨማሪ አክሲዮኖችን ሊሸጥ ይችላል። ይህን ደግሞ ሁለተኛ ዙር የአክሲዮን ሽያጭ (secondary market) ይባላል። ድርጅቱ በሁለተኛ ዙር ብቻ ሳይገደብ ለሦስተኛም ለአራተኛም... ወዘተ ጊዜ በስቶክ ማርኬት ላይ በመቅረብ አክሲዮኖቹን መሸጥ የሚችል ይሆናል። ምክንያቱም የተለየ ጉዳይ ካላጋጠመ በስተቀር ድርጅቱ በስቶክ ማርኬት ላይ አንዴ እስከተመዘገበ ድረስ ሌላ ምርመራ ወይም ጥናት መደረግ ሳያስፈልገው ገንዘብ በአስፈለገው ቁጥር የፈለገውን ያህል አክሲዮን ካለምንም ገደብ መሸጥ ስለሚችል ነው። ከዚህ ድርጅት አክሲዮን የገዙ ሌሎች ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች በማንኛውም ጊዜ ወደ ስቶክ ማርኬት በመሔድ አክሲዮኖቻቸውን መሸጥ የሚችሉ ሲሆን ይህም ሁለተኛ ዙር የአክሲዮን ሽያጭ ይባላል።

        የስቶክ ሻጮችንና ገዥዎችን በምንመለከትበት ጊዜ ድርጅቶች፣ ኩባንያዎች እንዲሁም ግለሰቦች ስቶክ ሊገዙም ሆነ ሊሸጡ ይችላሉ። ምክንያቱም ስቶክ ማርኬት የኢንቨስትመንት መሳሪያ በመሆኑ ድርጅቶች ትርፍ ገንዘብ (excess cash) ካላቸው ስቶክ በመግዛት ይህንን ትርፍ ገንዘባቸውን ወደ ኢንቨስትመንት በመለወጥ ውጤታማ መሆን ይችላሉ። በዚያው ልክ እንደገና ደግሞ ተቋማዊ ኢንቨስተሮች (Institutional investors) የምንላቸው ተቋማት ለምሳሌ እንደ ሙቹዋል ፈንድ፣ ..... ፈንድና ባንኮችም ጭምር በተቋማዊ ኢንቨስተርነት ይታወቃሉ። እነዚህ ተቋማት የፋይናንስ ተቋማት በመሆናቸውና ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ስላላቸው ስቶክ ማርኬት ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ተቋማት ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ተቋማት "ኢንስቲትዮሽናል ኢንቨስተርስ" እንላቸዋለን። በግለሰብ ደረጃ ስቶክ የሚገዙትን ደግሞ "ኢንዲቪዡዋል ኢንቨስተርስ" እንላቸዋለን ማለት ነው። እነዚህ ሁለት አካላት ስቶክ መግዛት ብቻም ሳይሆን መሸጥም ይችላሉ።

    ወደ ስቶክ ግብይቱ ስንመጣ ደግሞ የስቶክ ገዥውንና ሻጩን የሚያገናኝ ማዕከል ወይም ማርኬት ያለ ሲሆን ይህ ተቋም በህግ ደረጃ የተቋቋመና የስቶኩን ዋጋ የሚቆጣጠርና የሚያጠና ተቋም ነው። በተለይ ደግሞ በዚህ ተቋም ውስጥ ይህንን ስራ የሚሰሩና ግብይቱን የሚያሳልጡ "market makers or specialists" የሚባሉ አካላት አሉ። ስለዚህ በዚህ የግብይት ስርዓት ውስጥ ስቶክ ሻጮች፣ ገዥዎችና ገበያው (market) አሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በጥቅል ስሙ ስቶክ ማርኬት እየተባለ ይጠራል። ይህንን ካልን ዘንዳ በስቶክ ግብይት ውስጥ ገዥና ሻጭ በቀጥታ ተገናኝተው ንግድ አይለዋወጡም፤ መገናኘትም አንጠበቅባቸውም። ይህንን በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ የመኪና ግብይትን ብንወስድ መኪናውን የሚሸጠውና የሚገዛው አካል እንዳለ ሁሉ በስቶክ ማርኬትም ውስጥ እንደዚያው ነው። ይሁን እንጂ ስቶክ ማርኬትን ለየት የሚያደርገው ገዥና ሻጭ በአካል አይገናኙ፣ አይተዋወቁምም መተዋወቅም አያስፈልጋቸውም። ይህ ከሆነ ስቶክ ሻጮችና ገዥዎች እንዴት ነው ተገናኝተው የሚገበያዩት? በምንልበት ጊዜ እነዚህ አካላት በስቶክ ደላሎች (stock brokers) አማካኝነት የስቶክ ልውውጡ ይከናወናል ማለት ነው። እነዚህ ደላሎች ከዚህ ቀደም እንደምናውቃቸው ዓይነት ደላሎች ሳይሆኑ ህጋዊነታቸው የተረጋገጠ፤ በቂ የሆነ የፋይናንስ ዕውቀት ያላቸው፤ በስብዕናቸው ምስጉን የሆኑና ታማኞች ሆነው ከስቶክ ማርኬቱ ጋር ቅርብ ሆነው የገዥውንና የሻጩን ፍላጎት ሪፖርት የሚያቀርቡ አካላት ናቸው። ድርጅቶች፣ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ስቶኮችን በሸጡና በገዙ ቁጥር ደላሎቹ ኮሚሽን የሚታሰብላቸው ይሆናል። የስቶክ ደላሎች በስቶክ ግብይቱ ውስጥ ያላቸው አስፈላጊነት በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሲሆን የመጀመሪያው አስፈላጊነታቸው ለስቶክ ገዥዎችና ሻጮች እንደ አማካሪ (advisor) በመሆን ሲያገለግሉ፤ ሁለተኛው ጠቀሜታቸው ደግሞ የስቶክ ገዥዎቹና ሻጮቹ ትክክለኛና ህጋዊ መሆናቸውን ማረጋገጥና ለስቶክ ግብይት ተቆጣጣሪው አካል (market makers) ሪፖርት ማቅረብ ነው። ምክንያቱም አንዳንዶች ገንዘብ ሳይኖራቸው ስቶክ ለመግዛት ይሔዳሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ በስቶክ ማርኬቱ ላይ ሳይመዘገቡና የስቶክ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርትፊኬት ሳይኖራቸው ስቶክ ለመሸጥ የሚሞክሩ አጭበርባሪ አካላት በመኖራቸው የተነሳ ነው።

    የስቶክ ደላሎች የገዥንና የሻጭን ፍላጎት በመቀበል ለስቶክ ግብይት ተቆጣጣሪው አካል ሪፖርት ያደርጋሉ። ይህም ሲባል ለምሳሌ በገዥው በኩል ያለው ደላላ ደንበኛው ባዘዘው መሰረት ማለትም መግዛት የሚፈልገውን የአክሲዮን ብዛት፤ የየትኛውን ኩባንያ እንደሆነና መግዛት የሚፈልጉበትን የዋጋ ተመን የያዘ የግዥ ትዕዛዝ መረጃ ለስቶክ ማርኬት ያቀርባሉ ማለት ነው። በሻጩ በኩልም ያለው ደላላ እንደዚሁ ሻጩ መሸጥ የሚፈልገውን የአክሲዮን ብዛት፤ የኩባንያውን ስምና የሽያጩን  የዋጋ ተመን የያዘ መረጃ ለስቶክ ማርኬቱ ተቆጣጣሪ አካል የሽያጭ ትዕዛዝን ያቀርባሉ ማለት ነው። ስለዚህ ስቶክ ማርኬት ሁለት መረጃዎች ወይም ሪፖርቶች ይደርሱታል ማለት ነው። ከገዥው በኩል ካለው ደላላ የሚመጣ ሪፖርትና ከሻጩ በኩል ካለው ደላላ የሚመጣ የሽያጭ ሪፖርት ማለት ነው። ከዚያም የስቶክ ግብይት ተቆጣጣሪው አካል ሁለቱን ራፖርቶች በማመሳከርና በማጣጣም (matching) ሽያጩን ካከናወኑ በኋላ ወደ ባለቤትነት አዘዋዋሪ አካል (clearing house) በማስተላለፍ የሻጩን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርትፊኬት ወደ ገዥው አካል የስም ዝውውር ይደረግለታል ማለት ነው። የክፍያው ሁኔታ ደግሞ በገዥው ደላላ አማካኝነት ገንዘቡን ወደ ሻጩ አካውንት እንዲተላለፍ ይደረጋል። ስለዚህ የባለቤትነት ስም በሚያዘዋውረው አካል (clearing house) ውስጥ ሁለት ነገሮች ይከናወናሉ ማለት ነው። የመጀመሪያው ህጋዊ የባለቤትነት ሰርትፊኬት ዝውውርና የክፍያ አፈፃፀም ናቸው። ይህ ደግሞ በራሱ የሚወስደው ጊዜ አለ። ለምሳሌ በአሜሪካው ስቶክ ማርኬት (ናዝዳክ) ይህ የየባለቤትነት የስም ዝውውርና የክፍያ ሒደት 72 ሰዓታት ወይም ሦስት ቀናትን ይፈጃል። እንግዲህ በእኛ አገር ይህ ሒደት ምን ያህል ቀን እንደሚፈጅ አብረን የምንመለከተው ይሆናል።

    በአጠቃላይ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ስቶክ የማገዙ፣ የሚሸጡ፣ የሚያሻሽጡ ደላሎች፣ የገዥንና የሻጭን ሪፖርቶች የሚያመሳክሩና የሚያቆራኙ (market makers) እና በመጨረሻም የባለቤትነት ስም ዝውውር የሚያደርጉና የክፍያ አፈፃፀም የሚያደርገው አካል (clearing house) አሉ። ይህንን የግብይት ሰንሰለት ወይም ስርዓት የሚቆጣጠር ህጋዊ አካል ያለ ሲሆን ይህም ተቋም ህጋዊ የአክሲዮን ተቆጣጣሪ አካል (security exchange commission) ነው። ይህ ተቋም በአብዛኛው በመንግሥት ደረጃ የሚቋቋም ሲሆን በተቀረፀለት ህግና ደንብ አማካኝነት የሻጩንና የገዥውን ደህንነት ያረጋግጣል፤ በስቶክ ግብይቱ ውስጥ የተመዘገቡ ወይም ለመመዝገብ የሚመጡ ኩባንያዎች፣ ድርጅቶችና ተቋማት የፋይናንስ ሪፖርታቸው የራሳቸውን የስቶክ ዋጋ በሚጨምር መልኩ አዘጋጅተው ማቅረብ አለማቅረባቸውንና የፋይናንስ ሪፖርቱን ጤናማነት ያረጋግጣል፤ የስቶክ ደላሎቹንም ህጋዊነት፤ በፋይናንሱ ረገድ ያላቸውን ዕውቀትና ስብዕናቸውን ይፈትሻል ያረጋግጣልም። ምክንያቱም የስቶክ ደላሎች አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ የኮሚሽን ክፍያ ለማግኘት በማሰብ አላስፈላጊና ከህግ ማዕቀፉ ውጭ የሆኑ የስቶክ ግዥዎችንና ሽያጮችን ሊያከናውኑ ስለሚችሉ ነው ይህን መሰል ቁጥጥር ማድረግ ያስፈለገው ማለት ነው። ከዚህም ባሻገር ይህ የአክሲዮን ተቆጣጣሪ ተቋም የባለቤትነት ስም አዘዋዋሪውንና የክፍያ አስፈፃሚውን አካል፤ የሂሳብ አዋቂዎች (auditors) የፋይናንስ ሪፖርቶችን በትክክልና በታማኝነት ኦዲት ማድረጋቸውንና በስቶክ ማርኬቱ ውሰጥ የሚሳተፉትን ባለሙያዎች የትምህርት ደረጃና የስራ ፈቃድ ትክክለኛነት ያረጋግጣል ማለት ነው። ስለዚህ የስቶክ ግብይቱ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሁም ተዓማኒ ይሆን ዘንድ ይህ የአክሲዮን ተቆጣጣሪ አካል (security exchange commission) ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል። በአጠቃላይ ስቶክ ማርኬት የሚባለው እነዚህን ሁሉ አካላት በውስጡ ያካተተ የገበያ ስርዓት ነው ማለት ነው። ❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤