በስቶክ ማርኬት ኢንቨስትመንት ላይ ውጤታማ ለመሆን በሚገባ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ከእነዚህ ዝግጅቶች ውስጥ ደግሞ አራት መሰረታዊ ነገሮች ሊኖሩን ያስፈልጋል ማለት ነው። ምክንያቱም ስቶክ ማርኬት እንዲህ በቀላሉ ገንዘብ ኢንቨስት አድርገን በቀላሉ ውጤታማ ልንሆንበት የሚያስችለን የኢንቨስትመንት ዘርፍ አይደለምና። በዚህ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በቀላሉ ውጤታማ ልንሆንባቸውና ቀላልም የማይሆንባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ስለዚህ በዚህ የግብይት ስርዓት ውስጥ ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት እነዚህ አራት መሰረታዊ ነገሮች ሊኖሩን ይገባል። ካልሆነ ግን ለኪሳራ እንዳረጋለን ማለት ነው።

በስቶክ ማርኬት ኢንቨስትመንት ላይ ውጤታማ ሊያደርጉን የሚችሉትን ነገሮች በእንግሊዘኛው አጠራር በአራት "E" ዎች ከፍለን እናያቸዋለን። የመጀመሪያው E (Excess cash) ወይም የትርፍ ገንዘብ መኖር የሚባለው ሲሆን ይህም ማለት ስሙ እንደሚያሳየው ለኑሯችን ከሚያስፈልገን ገንዘብ ውጭ የተቀመጠ ትርፍ ገንዘብ ማለት ነው። ምክንያቱም በስቶክ ማርኬት ላይ ኢንቨስት ስናደርግ ለኑሯችን ለተለያዩ ወጭዎች ከምናወጣ ገንዘብ ላይ ቀንሰን አይደለምና። ይህንን በሚገባ መገንዘብ አለብን። ምክንያቱም ከኢንቨስትመንቱ ተጠቃሚ ለመሆን ጊዜ (Holding period) ስለሚያስፈልግ ነው። ወዲያውኑ ትርፍ ማግኘት አይቻልም። ስለዚህ ከኑሮ ወጭያችን ላይ ቀንሰን ኢንቨስት የምናደርግ ከሆነ ለችግር እንጋለጣለን ማለት ነው። ይህም በመሆኑ በስቶክ ማርኬት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ለኑሮ ከሚያስፈልገን ወርሃዊም ሆነ ዓመታዊ ወጭዎቻችን ውጭ የሆነ ገንዘብ ማጠራቀም ወይም መቆጠብ ይኖርብናል ማለት ነው። ይህንን ትርፍ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ከገቢያችን በታች መኖርን መለማመድና በየወሩ የሚተርፈንን ገንዘብ በባንክ መቆጠብ መቻል ዋነኛው ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ በሚከፈተው የስቶክ ግብይት (stock exchange) ላይ ማንኛውም ሰው ባለው የገንዘብ አቅም ልክ መሳተፍ ይችላል። ይህም ማለት ማንኛውም ሰው ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ ባለው የገንዘብ መጠን ልክ ስቶኮችን ወይም አክሲዮኖችን በመግዛትና በገዛው የአክሲዮን መጠን ልክ ትርፍ ማግኘት ይችላል ማለት ነው። ነገር ግን ኢንቨስት የሚደረገው ገንዘብ ለዚሁ አላማ ብቻ ተብሎ የተዘጋጀ ትርፍ ገንዘብ (excess cash) መሆን ይኖርበታል። በስቶክ ማርኬት ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስፈልገው ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን ከ5 -10 ሺህ ብር (እንደየ አገራቱ ቢለያይም ይህ በእኛ አገር ሊሆን ይችላል የሚል ነው) ሲሆን ከፍተኛው የገንዘብ መጠን ግን ገደብ የለውም። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከአምስት ሺህ ብር ጀምሮ አክሲዮን በመግዛት መሳተፍ ይችላል ማለት ነው። በእርግጥ በስቶክ ግብይት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሱ አገሬት ውስጥ በሳንቲሞች ደረጃ ስቶክ በመግዛት መሳተፍ የሚችሉበት ሁኔታም አለ። ይህ ደግሞ "ፔኒ ስቶክ" በመባል ይታወቃል። ስቶክ ማርኬት በአገራችን በቅርቡ ሲጀመር እነዚህ "ፔኒ ስቶኮች" ይኖራሉ ብለን ባንጠብቅም ነገር ግን የስቶክ ገበያው ሲደራና ሲሟሟቅ ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን።

    በስቶክ ማርኬት ላይ ውጤታማ ከሚያደርጉን 4E's መካከል ሁለተኛውና መሰረታዊው E (Education) ወይም ዕውቀትነው። ዕውቀት ሲባል የምን ዕውቀት ነው? በምንልበት ጊዜ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ለመሳተፍ ወይም ኢንቨስት ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ስቶክ ማርኬት ምንነትና ስለ ገበያ ስርዓቱ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ መኖር ማለት ነው። በስቶክ ማርኬት ዙሪያ የተሻለ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች በጣም ትርፋማና ውጤታማ መሆን ሲችሉ በአንፃሩ ደግሞ ስለ ስቶክ ምንነትና ሰለ አሰራሩ ግንዛቤውና ዕውቀቱ የሌላቸው ሰዎች የመክሰር ዕድላቸው በጣሙን ሰፊ ነው። እነዚህ ሰዎች ካለ በቂ ዕውቀት በስቶክ ማርኬት ውስጥ የሚሳተፉ ከሆነ ነገሩ የሚሆነው እንደ ሎተሪ ዕጣ ነው። ይህም ማለት የሎተሪ ዕጣ ከብዙ ሚሊዮን ባለ ዕድሎች ዕጣው የሚወጣላቸው ከሁለት ወይም ከሶስት ለማይበልጡ ሰዎች ብቻ በመሆኑ የተነሳ አሸናፊ የመሆን ዕድሉ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ሁሉ በስቶክ ማርኬትም ውስጥ በርካቶች ካለ በቂ ዕውቀት ዘው ብሎ መግባት የመክሰር ዕድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ሀብትን እስከ ወዲያኛው የማጣትን ዋጋ ያስከፍላል ማለት ነው። በርካቶች እንደውም ሃብታቸውን ብቻም ሳይሆን የሚያጡት ህይወታቸውንም ጭምር አጥተዋል። ስለዚህ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ኢንቨስት አድርገን ራሳችንን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና ውጤታማ ለመሆን ስለ ስቶክ ማርኬት በቂ የሆነ የዕውቀት ስንቅ መያዝ ይኖርብናል ማለት ነው። ምክንያቱም ስቶክ ማርኬት እንዲህ በቀላሉ እንደ ማንኛውም ኢንቨስትመንት ውጤታማ መሆን የምንችልበት የግብይት ስርዓት አይደለምና። ለዚህ ደግሞ ምን ያስፈልጋል? በምንልበት ጊዜ የመጀመሪያው ጉዳይ በተለይ በፋይናንስ ትንታኔ (financial analysis) ማለትም የድርጅቶቹን ወይም የካምፓኒዎቹን የፋይናንስ ሪፖርት ማንበብ መቻል ነው። ይህንን ስናደርግ በዋናነት የሚጠቅመን የተሻለ የፋይናንስ አፈፃፀም፣ ጠንካራ፣ ውጤታማ እንዲሁም አትራፊ የሆነውን ድርጅት መርጠን ኢንቨስት እንድናደርግ ስለሚያስችለን ነው። ምክንያቱም ደካማ የፋይናንስ አፈፃፀም ባለው ድርጅት ላይ ኢንቨስት ካደረግን ወይም ድርጅቱ ለሽያጭ ያቀረባቸውን አክሲዮኖች ከገዛን የመክሰር ዕድላችን ከፍተኛ ነው የሚሆነው። ከፍተኛ ገቢ ያለው፤ በገበያው ላይ የመሪነትና ከፍተኛ የተወዳዳሪነት አቅም ያለው፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ የሆነ፤ ከአሁን ቀደም የተሻለ የፋይናንስ አፈፃፀም (excellent track record) ያለውን ድርጅት መምረጥና ኢንቨስት የምናደርግ መሆን መቻል አለብን። ስለዚህ አንድ ድርጅት ወይም ካምፓኒ ከሌላኛው ድርጅት የተሻለ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን የመጀመሪያውና ቁልፉ ነገር የድርጅቶቹን የፋይናንስ ሪፖርት ማንበብ መቻል አለብን ማለት ነው። ፋይናንሻል ሪፖርት ሲባል ሦስት ዓይነት የፋይናንስ ሪፖርቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም የድርጅቱ የገቢና ወጭ ሪፖርት (Income statement)፤ የትርፍና ኪሳራ መግለጫ (Balance sheet) እንዲሁም ደግሞ የሀብትና የዕዳ ሚዛን የሚያሳይ ሪፖርት (cash flow) ናቸው። ስለዚህ ማንኛውም ሰው በስቶክ ማርኬት ውስጥ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት የድርጅቶቹን አጠቃላይ የፋይናንስ አፈፃፀም በሚገባ ማንበብ አለባቸው ማለት ነው። ስለዚህ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ለመሳተፍ ከሚያስፈልጉን የዕውቀት ስንቆች አንዱ የድርጅቶቹን የፋይናንስ ሪፖርት ማንበብ መቻል ነው።

     በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምናገኘው ደግሞ የኢንደስትሪ ትንታኔ (Industrial analysis) ዕውቀት ነው። ይህም ማለት የአንድ ድርጅት ውጤታማነት ከንግድ ዘርፉ ውጤታማነት ጋር የተያያዘ ከመሆኑ የተነሳ የንግድ ዘርፉ ውጤታማነት ምን ያህል ነው? በጣም አዋጭ ነው ወይስ አይደለም? ጠንካራ ተወዳዳሪዎች ያሉበት የንግድ ዘርፍ ነው ወይስ አይደለም (ማለትም ትርፋማነቱ አመርቂ የሆነ የንግድ ዘርፍ ነው ወይስ አይደለም?)፤ እያደገ የሚሔድ ገቢ ያለውና ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው የንግድ ዘርፍ ሆኖ ነገር ግን ጠንካራ ተወዳዳሪዎች የሌሉበት ወይም ክፍተት ያለው የንግድ ዘርፍ ስለሆነ በዚያ ደረጃ ኢንቨስት የተደረገበት ኩባንያ በዚህ ኢንደስትሪ ውስጥ የማደግ ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል ብለን ለመደምደምና ለመወሰን የኢንደስትሪ ትንታኔ (Industrial analysis) በእጅጉ ያስፈልገናል ማለት ነው።

     በስቶክ ማርኬት ውስጥ ስኬታማ ለመሆን ከሚያስፈልጉን ዕውቀቶች በሦስተኛ ደረጃ ላይ የምናገኘው ደግሞ የኢኮኖሚ ትንታኔ (Economic analysis) ነው። የአንድ አገር ኢኮኖሚና ስቶክ ማርኬት በጣም የተያያዙ በመሆናቸው የአንድ አገር ኢኮኖሚ ባደገ ቁጥር የስቶክ ግብይቱም በጣም እያደገና ተፈላጊነቱም እየጨመረ ይመጣል። ለምሳሌ አንድ ሰው የሚፈልገውን አክሲዮን ለመሸጥ ቢፈልግ ወዲያውኑ በሚፈልገው ዋጋ አትርፎ መሸጥ ይችል ዘንድ ያደርገዋል። በአንፃሩ ደግሞ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዝቅተኛ በሆነ ቁጥር የስቶክ ግብይቱም እየወረደና ተፈላጊነቱም እየቀነሰ የሚሔድ ይሆናል ማለት ነው። ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል የተለያዩ ነገሮች እንደ ምክንያት የሚጠቀሱ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ግን የዋጋ ግሽበት (Inflation rate)፤ የወለድ ምጣኔ (Interest rate) እና የውጭ ምንዛሬ ተመንና ክምችት (Foreign exchange rate) የአንድን አገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚወስኑ ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ የባንኮች የወለድ ምጣኔ መቀነስና መጨመር፤ የውጭ ምንዛሬ መጨመርና መቀነስ እንዲሁም የወጋ ግሽበቱ መጨመር በስቶክ ግብይቱ ላይ ዓይነተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። ይህም ማለት ስቶኮችን መቼ መግዛትና መሸጥ እንዳለብን ለመወሰን የአንድ አገር ኢኮኖሚ መውጣትና መውረድ ይወስነዋል ማለት ነው። ስለዚህ በየትኛው የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ነው ተጠቃሚ ልንሆን የምንችለው? የሚለውን ጉዳይ ለማወቅ የኢኮኖሚ ትንታኔ (Economic analysis) ዕውቀት ያስፈልገናል ማለት ነው።

    ሌላኛው የሚያስፈልገን ዕውቀት ደግሞ ስቶኮቻችንን መቼ መግዛትና መሸጥ እንዳለብን የመወሰን ጥበብ ነው። ይህንን ለመወሰን ደግሞ የገበያውን እንቅስቃሴ መለየት ያስፈልጋል። የግብይት ውሎው ምን ይመስላል፤ የገበያው እንቅስቃሴ እያደገ መሆን አለመሆኑን፤ የስቶክ ጠቋሚዎቹ (stock indexes) በየሰዓቱና በየዕለቱ የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች በማየት ውሳኔ ማሳለፍ ያስፈልጋል። በእርግጥ በተለያዩ አገራት ያሉ የስቶክ ግብይቶች የራሳቸው የሆነ የገበያ ውሎ ጠቋሚ (stock indexes) አሏቸው። ለምሳሌ በአሜሪካ ስቶክ ማርኬት ውስጥ "ናዝዳክ ኢንዴክስስ"፤ በጃፓን ደግሞ "225 ኢንዴክስ" በሎንዶን ደግሞ ".... ሃንድረድ" የተሰኙ የስቶክ ውሎ ጠቋሚ ኢንዴክሶች አሏቸው። የስቶክ ኢንዴክስ የምንላቸው የዕለቱን የስቶክ ግብይት ውሎ ሪፖርት የሚያደርጉ ናቸው። የስቶክ ግብይቱ ዛሬ ወርዷል፤ ከፍ ብሏል እያሉ ሪፖርት ያደርጋሉ ማለት ነው። ስለዚህ ይህን የመውጣትና የመውረድ ነገር ማወቅና መተንተን ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህ ዕለታዊ ሪፖርት ስቶኮቻችንን መቼ መግዛትና መሸጥ እንዳለብን ለመወሰን ጥቆማ ስለሚሰጡን ነው። ምክንያቱም ስቶክ ማርኬት ላይ የሚመከረው በዝቅተኛ ዋጋ መግዛትና በከፍተኛ ዋጋ መሸጥ ነውና። ስለዚህ ስቶኮችን በዝቅተኛ ዋጋ ለመግዛትም ሆነ በከፍተኛ ዋጋ መቼ መሸጥ እንዳለብን ለመወሰን ስቶክ ኢንዴክሶች በየዕለቱ የሚያቀርቡትን ሪፖርት ማዳመጥና መተንተን ያስፈልጋል። ስለዚህ ይህ ዕውቀት የሚጠቅመን በስቶክ መግዛትና መሸጥ ላይ ትክክለኛ ውሳኔ ለማሳለፍ ነው ማለት ነው።

     ሦስተኛውና መሰረታዊው E ደግሞ (Experience) ወይም ልምድ የሚባለው ነው። በስቶክ ማርኬት ኢንቨስትመንት ላይ የካበተ ልምድ ካለን የተሻለና ውጤታማ ኢንቨስተር መሆን እንችላለን ማለት ነው። በዚህም የተነሳ በዚህ የገበያ ስርዓት ውስጥ ያለን ልምድ እየዳበረ በሔደ ቁጥር ውጤታማነታችንም በዚያው ልክ  እየጨመረ ይሔዳል። አብዛኞቻችን ደግሞ ለስቶክ ማርኬት አዲስ እንደመሆናችን መጠን ልምዳችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳበርን መሔድ ይኖርብናል ማለት ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ ትክክለኛ ውሳኔ የመወሰን ዕድላችን ያድጋል። ለምሳሌ አንድ ሰው መንጃ ፈቃድ ስላወጣ ብቻ ጥሩ ሹፌር ይሆናል ማለት አይደለም። በጊዜ ሒደት ነው ልምድ እየቀሰመና እያዳበረ በመሔድ ጥሩ ሹፌር የመሆንና ስህተት የመስራት ዕድሉን ይበልጥ እየቀነሰ የሚመመጣው። በስቶክ ማርኬትም ውስጥ እንዲሁ ውጤታማ ኢንቨስተር ለመሆን ልምድ ማካበት ያስፈልጋል ማለት ነው። በተለይ ደግሞ በስቶክ ግብይት ውስጥ ልምድ ከማካበት አንፃር በኢትዮጵያ ንግድ ገበያ (ECX) ላይ የተሳተፋችሁ ነጋዴዎች በዚያ ያዳበራችሁትን ልምድ ወደ ስቶክ ማርኬት ማምጣት ትችላላችሁ። ምክንያቱም በECX ውስጥ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ የቡና... ወዘተ. የንግድ ልውጦጦች ከመደረጋቸውና በአዲስ አበባ ስቶክ ውስጥ ደግሞ የአክሲዮን ወይም የስቶክ ግብይቶች ከመደረጋቸው ውጭ በመርህ ደረጃ ተመሳሳይ የግብይት ስርዓት ነውና ያላቸው።

      አራተኛውና የመጨረሻው E ደግሞ (Emotional discipline) ወይም ደግሞ ስሜትን የመቆጣጠር ብቃት ነው። ይህም ማለት በስቶክ ማርኬት ውስጥ በጣም ትርፋማ መሆንና እንዲሁም ደግሞ ልንከስርም እንችላለን። ስለዚህ ትርፋማ ስንሆን በጣም ልንደሰትም ሆነ፤ ስንከስር ደግሞ በሃዘን መቆራመድ የለብንም። ምክንያቱም እነዚህ ሁለት ዋልታ ረገጥ ስሜቶች በስቶክ ማርኬት ውስጥ ሁልጊዜም ይኖራሉና። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የስሜት ቁጥጥር ብቃት ሊኖረን ይገባል ማለት ነው።

 ❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤