የአንድን አገር ኢኮኖሚ የምንለካባቸው በርካታ መስፈርቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መለኪያዎች ውስጥ በዋናነት የምንመለከተው የአገራዊ ጥቅል የኢኮኖሚ ምርታማነትን (GDP) ነው። በአንድ አገር ስቶክ ማርኬት ባለ ቁጥር የካፒታል ምርታማነት ይጨምራል፤ ብዙ ድርጅቶች ደግሞ ገንዘብ የሚያገኙባቸው አማራጮች ይሰፋሉ ማለት ነው። ከዚህ ቀደም ድርጅቶች ገንዘብ የሚያገኙት ከባንኮች በመበደር ብቻ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ነገር ግን ስቶክ ማርኬት ሲመጣ ድርጅቶቹ አክሲዮናቸውንና ኮርፖሬት ቦንድ አዘጋጅተው በመሸጥ በብድር መልክ ገንዘብ ማግኘት የሚችሉ ይሆናል። ለምሳሌ የስቶክ ማርኬት ሽያጫቸው ከፍተኛ በሆኑባቸው አገራት ላይ ኩባንያዎች ከባንኮች በላይ ቦንድ በመሸጥ ገንዘብ የማግኘት ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። እንግዲህ አንድ ድርጅት ፋይናንስ ባገኘ ቁጥር፤ ወይም ደግሞ ለመክፈል የማያስገድዱ የገንዘብ ምንጮችን ድርጅቶች ባገኙ ቁጥር ምርታቸውና ተወዳዳሪነታቸው ይጨምራል። በዓለም አቀፍ ደረጃም ጥሩ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ስቶክ ማርኬት ከፍተኛውን ሚና በመጫወት የአንድን አገር ኢኮኖሚና የምርታማነት መጠን ያሳድጋል ማለት ነው። የአንድ አገር ኢኮኖሚ ባደገ ቁጥር ደግሞ የዜጎች የነፍስወከፍ ገቢ ይጨምራል፤ ይህ ሲሆን ደግሞ የዜጎች የኑሮ ደረጃ በጣም ይሻሻላል ማለት ነው። ስለዚህ ከአሁን ቀደም አንድ ለእናቱ የነበረውን የፋይናንስ ምንጭ ወደ ሁለት ከፍ በማድረግ ስቶክ ማርኬት ጉልህ ሚና ይጫወታል። ይህ ሲሆን ደግሞ ብዙ አዳጊ ድርጅቶች፤ ብዙ ስራ ፈጣሪዎችና በርካታ አዳዲስ ድርጅቶች ገንዘብ የማግኘት ዕድላቸው ስለሚሰፋ ወደ ትልልቅ ካምፓኒነት የማደግ ዕድላቸው እንዲሁ ይሰፋል ማለት ነው። በዚህም የተነሳ በአንድ አገር ጥቅል ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ዕድገት ከፍተኛ ይሆናል። ይህ እንግዲህ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈፃፀም አንፃር የምንመለከተው ነው።

   ሌላው በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ድርጅቶችና ተቋማት ምርታማነታቸው ባደገ ቁጥር የሰራተኞች የክፍያ መጠን ይጨምራል ማለት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን እውነተኛው የደመወዝ ዕድገት (real wealth rate) መጠን እንዲሁ ይጨምራል ማለት ነው። ይህ የሚጨምረው እንዴት ነው? በምንልበት ጊዜ የአንድ አገር ምርታማነትና የኮርፖሬት ኢፊሸንሲ በጨመረ ቁጥር በአገሪቱ ላይ ያለው የግሽበት መጠን(inflation rate) እየቀነሰ ስለሚመጣ ነው። ምክንያቱም የማምረት መጠን የሚጨምር በመሆኑ ብዙ ባመረትን ቁጥርና ወጭን የመቆጣጠር ዕድል ከፍተኛ ስለሚሆን ምርቶች በአነስተኛ ዋጋ ለገበያ የሚቀርቡበት ዕድል ከፍተኛ ይሆናልና ነው። ይህ ማለት ደግሞ ስቶክ ማርኬት የኑሮ ውድነትን እንዲቀንስ በማድረጉ ረገድም ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል ማለት ነው። ስለዚህ የኑሮ ውድነት መቀነስና የደመወዝ ዕድገት በአንድ ላይ ሲጣመሩ ደግሞ የእውነተኛ ደመወዝ (real wealth rate) መጠን በጣም የሚያድግ ይሆናል። ምክንያቱም የዋጋ ግሽበት ባለበት ሁኔታ የደመወዝ ዕድገቱ በምንም ያህል መጠን ቢጨምርም የመግዛት አቅም እስከሌለው ድረስ ጥቅም የለውም። ለዚያም ነው የኑሮ ውድነት መቀነስና የእውነተኛ ደመወዝ (real wealth rate) ክፍያ መጠን መጨመር አብረው ጎን ለጎን መሔድ ያለባቸው። ይህ የሚሆነው ደግሞ በስቶክ ማርኬት ላይ ነው ማለት ነው።

   በስቶክ ማርኬት ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ባስመዘገቡት አገራት ላይ የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው በማህበረሰብ ደረጃ ድርጊቶች ወይም ሐሳቦች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ባህል እያደገ የመጣበትን ሁኔታ ነው። ወደ አገራችን በምንመጣበት ጊዜ ደግሞ ሁለት ዓይነት የኢንቨስትመንት አማራጮች ናቸው ያሉት። አንደኛው ቢዝነስ መስራት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ገንዘብን በባንክ በመቆጠብ የሚገኘው ወለድ ነው። በዚህም የተነሳ በአገራችን በአሁኑ ወቅት የተሻለ ኑሮ የሚኖሩት አንድም ቢዝነስ የሚሰሩትና ሁለትም ተቀጥረው ከመስራት ባሻገር ገንዘባቸውን የሚቆጥቡት ናቸው። ይህንን በሌላ መንገድ ስንመለከተው ቢዝነስ መስራትን በሁለት አይነት መንገድ እናየዋለን። ይኸውም ምርትና አገልግሎትን በመሸጥ ቢዝነስ መስራትና በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ቢዝነስ መስራት ናቸው። ነገር ግን ማንኛውም ሰው በቀላሉ ኢንቨስት ሊያደርግባቸው የሚችሉ መሳሪያዎች ደግሞ ያስፈልጋሉ። ለምሳሌ 200 ሺህ ብር ያለው ሰው ቢዝነስ ልስራ ቢል በተለይ ደግሞ ግለሰቡ ተቀጥሮ የሚሰራ ከሆነ ይቸገራል። ምክንያቱም በአንድ በኩል ስራው አለ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ብር ምን ዓይነት ቢዝነስ ነው ልሰራ የምችለው? ብሎ ሲያስብ ግራ ስለሚገባው ሊያደርገው የሚችለው ነገር የግድ ገንዘቡን በመቆጠብ በሚያገኘው ወለድ ስለመጠቀም ማሰብ ነው። ይህ አማራጭ ደግሞ ከባንክ የሚያገኘው ወለድ ያን ያህል የኑሮ ውድነቱን የሚቋቋም ባለመሆኑ ይህም የገንዘብ ደህንነቱን ከማስጠበቅ በስተቀር አመርቂ አይሆንም። በዚህም የተነሳ በአገራችን በትንሽ ገንዘብ ወይም ተቀጣሪ ሰራተኞች ሆነው ቢዝነስ ለመስራት የሚያስችል ሁነኛ አማራጭ የለም። ስቶክ ማርኬት በሚመጣበት ጊዜ ግን አንድ ሰው በአቅሙ ልክ ስቶክ ወይም ቦንድ በመግዛትና ኢንቨስት በማድረግ በባንክ ቆጥቦ ከሚያገኘው ወለድ በላይ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘት ይችላል ማለት ነው። ይህ በመሆኑ ደግሞ ለማህበረሰቡ የተሻለ የኑሮ ደረጃ በማምጣትና ሀብታቸው እንዲያድግ በማድረግ ወደፊት በትርፍ ክፍፍል መልክ ገንዘብ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። እንዲሁም ደግሞ በጡረታ ዘመን ላይ ከገዙት አክሲዮን ወይም ቦንድ ከትርፍ ክፍፍል በሚያገኙት ገንዘብ የጡረታ ጊዜያቸውን ያለጭንቀት ማሳለፍ ይቻላቸዋል ማለት ነው። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የጡረታ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከድርጅቶቻቸው በሚቆረጥላቸው አነስተኛ ገንዘብ በመሆኑና ይህ ደግሞ አሁን ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት የሚቋቋም ባለመሆኑ ችግር ላይ ሲወድቁ ይስተዋላልና ነው። ስለዚህ የስቶክ ማርኬት መምጣት አማራጭ የኢንቨስትመንት ስልት ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ለማህበረሰቡ ሁነኛ የቢዝነስ አማራጭ በመሆን ከፍተኛውን ሚና ይወጣል።

   ሌላኛው የስቶክ ማርኬት ጠቀሜታ ደግሞ ትንንሽ ወይም አዳጊ ድርጅቶች ፋይናንስ ስለሚያገኙ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ አዳዲስ ድርጅቶች እንዲጎለብቱ፤ አዳዲስ ስራ ፈጠራዎች እንዲበራከቱ ያደርጋል። ትንንሽ ድርጅቶች ገንዘብ ባገኙ ቁጥር ደግሞ ራሳቸውን ከማሻሻልም አልፈው ለበርካቶች የስራ ዕድልን ይፈጥራሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የስራ አጥ ቁጥር ይቀንሳል ማለት ነው። ኢኮኖሚያቸው ካፒታል ማርኬት መር በሆኑ አገራት ላይ የተጠናው ጥናት የሚያሳየውም ይህንኑ ነው። ከዚህ አንፃር በአገራችን በአሁኑ ወቅት ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ካየነው በርካታ ምሩቃን ወጣቶች ያለ ስራ በቤታቸው የሚውሉበት፤ አብዛኛው ወጣት ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ ስደትን እንደ አማራጭ የኢኮኖሚ ምንጭነት የወሰደበት ሁኔታ ትልቅ ማሳያ ነው። ስለዚህ የስራ ዕድል ይኖር ዘንድ አማራጭ የቢዝነስ ዘርፍ በተፈጠረ ቁጥር በርካቶች ስራ የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ ስቶክ ማርኬት በሚመጣበት ጊዜ የሰራተኞችን እውነተኛ የደመወዝ ዕድገት መጠን ያሳድገዋል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የስራ ዕድል ፈጠራን በመጨመር የስራ አጡን ቁጥር በመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው ድርሻ በእጅጉ የጎላ ነው። የአገራችን ፖለቲካ ከኢኮኖሚያችን፣ ከኑሮ ውድነት እንዲሁም ከስራ አጥነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ ለፖለቲካዊ መረጋጋትም እነዚህ ሁለት ነገሮች ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ለመገንዘብ አያዳግትም።

   በሌላ መልኩ ደግሞ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ከማነቃቃት አንፃር ማክሮ ኢኮኖሚን ስንመለከተው ማክሮ ኢኮኖሚ የአንድ አገር ኢኮኖሚ የመዋዥቅ፣ የመቀነስ ወይም ደግሞ ተከታታይነት ያለው የዕድገት መቆም ደረጃ (negative growth rate) የሚገባባቸው ሁኔታዎችም አሉ። የአንድ አገር ኢኮኖሚ ያድጋል፣ ይሟሟቃል እንዲሁም ደግሞ ይቀንሳል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት የኢኮኖሚ መዋዠቆች እንዳይፈጠሩ ስቶክ ማርኬት ትልቅ ጠቀሜታን ይሰጣል። በተለይ ስቶክ ማርኬት ባለባቸው አገራት የሚስተዋለው የኢኮኖሚ መዋዠቅ በአንፃራዊነት ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው። ይህ ለምን ሆነ? ብለን ስንጠይቅ ይህ ሊሆንበት የቻለው በሁለት ምክንያቶች ሲሆን አንደኛው ምክንያት ስቶክ ማርኬት የአንድን አገር ኢኮኖሚ መቀዝቀዙን ወይም መሟሟቁን ወዲያው የሚጠቁም በመሆኑና በተለይ ስቶክ ጠቋሚዎች (stock indexes) ዝቅ ያለ ኢኮኖሚን በሚያሳዩን ቁጥር የአንድ አገር ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ነው ማለት ነው። በመሆኑም የአንድ ስቶክ ማርኬት አፈፃፀም ዝቅ አለ ማለት ለፖሊሲ አውጭዎች የሚሰጠው ትልቅ መልዕክት አለ። በሌላ አገላለፅ ይህ ችግር እንዲፈታ ጥቆማን ይሰጣል ማለት ነው። ስቶክ ማርኬት በሌለበት ሁኔታ ግን የአንድን አገር የኢኮኖሚ መቀዝቀዝና መሟሟቅ የሚታወቀው ረጅም ጊዜ ከፈጀ በኋላና በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ነው። ለምሳሌ ሜትሮዎሎጂን በምናይበት ጊዜ የአየር ንብረቱን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ጥቆማ ስለሚሰጠን ከወዲሁ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄና ዝግጅት በማድረግ ሊደርስ ይችል የነበረውን አደጋ ለመከላከል ወይም አደጋውን ለመቀነስ እንችል ዘንድ እንደሚያደርገን ሁሉ፤ በተመሳሳይም ስቶክ ማርኬት የአንድ አገር የኢኮኖሚ ሜትሮዎሎጂ በመሆኑ የተነሳ ለፖሊሲ አውጭዎች አገሪቱ ያለችበትን የኢኮኖሚ ቁመና በመጠቆም እነዚህ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን የማሻሻያ እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል። ወይም ደግሞ የፖሊሲ አውጭዎቹ ትክክል ያልሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀርፀው ከሆነና ይህም በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ወዲያውኑ ማወቅ ስለሚችሉ የፖሊሲ ለውጥ አሊያም ማሻሻያ እንዲያደርጉ ጥቆማ ይሰጣቸዋል ማለት ነው። እንግዲህ በአገራችን የተለያዩ ፓሊሲዎች ሲወጡ እናያለን ነገር ግን ፖሊሲው ትልቅ ችግር ከፈጠረ በኋላ፤ ትልቅ ውድመት ካስከተለ በኋላ ነው እንደገና ተጠንቶ የሚቀየረው ወይም የሚሻሻለው። በዚህም የተነሳ በርካታ የአገር ሀብት ባክኗል፤ የአገሪቱንም ኢኮኖሚ ክፉኛ ጎድቶታል። ምክንያቱም ስቶክ ማርኬትን የመሰለ የገበያ ሲስተም ባለመዘርጋቱ የተነሳ ነው። ይህም በመሆኑ ችግር ያለባቸውን ፖሊሲዎች ወዲያውኑ ለመቀየር ወይም ለማሻሻል ሳንችል ብዙ ነገር እንድናጣ ሆኗል ማለት ነው። ስቶክ ማርኬት በሚመጣበት ጊዜ ግን ይህንን ሁሉ ችግር እንድንቀርፍ፤ የኢኮኖሚ መዋዠቅን (Economic Volatility) በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያቸውን በስቶክ ማርኬት ላይ በመሰረቱ አገራት ላይ በተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ መሰል ችግሮች እንደሌሉባቸው ነው።

  ሌላኛው የስቶክ ማርኬት ትሩፋት ደግሞ ብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻሉ ነው። ይህ እንደምን ይሆናል? ስንል ስቶክ ማርኬት ሲመጣ "የሞርጌጅ ፋይናንሲንግ" አብሮ የሚጨምር በመሆኑ ሲሆን እንዲሁም ደግሞ ሪልስቴቶችም በስቶክ ማርኬት ላይ የሚሳተፉበት ሁኔታ ስላለ የሪል ስቴት ባለቤትም መሆን ይችላሉ ማለት ነው። ይህም ሲባል ማንኛውም ግለሰብ አፓርታማዎችን ሳይገባ፤ ቪላ ቤቶችን ሳያንፅ በስቶክ ማርኬት ላይ ከሚሳተፉ የሪልስቴት ኢንቨስተሮች ላይ ስቶክ (አክሲዮን) በመግዛት በተዘዋዋሪ የሪልስቴት ባለቤት መሆን ይችላሉ ማለት ነው። ስለዚህ በስቶክ ማርኬት መምጣት የተነሳ "የሞርጌጅ ፋይናንሲንግ" ዕድሎች በመኖራቸው፤ የወለድ ምጣኔ የመዋዥቅ ዕድሉ አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ ባንኮችም የማበደር አቅማቸው ከፍ እንዲል ያደርጋል ማለት ነው። በተመሳሳይ መንገድ "በሞርጌጅ ፋይናንሲንግ" ገበያው የማደግ እድል ስለሚኖረው ብዙ ሰዎች በቀላል ብድር መልክ የቤት ባለቤት የመሆን ዕድልን ይዞልን የሚመጣ ይሆናል።

    ሌላው ደግሞ ከስቶክ ማርኬት ጋር ተያይዞ መንግስትን የምንመለከት ይሆናል። መንግስት በአገር ደረጃ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችንና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ገንዘብ ያስፈልገዋል። ታዲያ በዚህን ጊዜ መንግስት የሚያደርገው ነገር ምንድነው ከውጭ አገር ባንኮች ወይም አገራት ገንዘቡን መበደር፤ ከአገር ውስጥ ባንኮች መበደር አሊያም ደግሞ በመንግሥት ብዙውን ጊዜ እንደተለመደው ቦንዶችን አዘጋጅቶ መሸጥ ነው። እዚህ ላይ የታላቁን የህዳሴ ግድብን እንደ ምሳሌ ማየት ይቻላል። መንግስት ቦንድ የሚሸጠው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ብቻም ሳይሆን የበጀት ጉድለቶችንም ለመሙላት ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ እንደ አገር የካፒታል ምርታማነታችን ባደገ ቁጥርና የኢንቨስትመንት ቀጠናው አመቺ በሆነበት ሁኔታ፤ ስቶክ ማርኬት ሲመጣ ደግሞ የኪሳራ ዕድልን (ሪስክን) ለመቆጣጠር ከማስቻሉም ባለፈ የካፒታል ስርጭቱ አዋጭ በሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲዘዋወር የማድረግ ዕድልንም ይፈጥርልናል። በአጠቃላይ አገሪቱ ተመራጭ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንዲኖራት ያደርጋል ማለት ነው። ይህ በሆነ ቁጥር ደግሞ የካፒታል ፍሰት እንዲኖርም ያደርጋል። ይህም ሲባል ኢንቨስተሮች ከሌላ አገራት በመምጣት ካፒታላቸውን ፈሰስ ስለሚያደርጉ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ በስቶክ ማርኬት መጀመር የተነሳ ከአሁን ቀደም የነበራት የኢንቨስትመንት ተመራጭነት በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጨምር በርካታ ኢንቨስተሮች ኢንቨስት ለማድረግ ይመርጧታል ማለት ነው። ይህም ኢንቨስተሮቹ ከውጭ ሲመጡ ገንዘብ በዶላር ወይም በዩሮ ወይም በፓውንድ መልክ ይዘው ስለሚመጡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከፍ እንዲል ያደርገዋል። ይህም ሲሆን የአገሪቱ የኢኮኖሚ አፈፃፀም ደረጃ በእጅጉ ይጨምራል ማለት ነው። ከዚህም ባሻገር ከውጭ አበዳሪ ተቋማት ገንዘብ የመበደር አቅሟ ይጎለብታል። ምክንያቱም ተበድራ የመመለስ አቅሟና ታማኝነቷ በዚያው መጠን ስለሚጨምር ነው።

   የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ ደግሞ በአገራችን ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በእጅጉ አናሳ መሆንና ያለውንም በፍትሐዊነት አለመጠቀም ምን ያህል የኢኮኖሚያችን ማነቆ ሆኖ እንደቆየ የሚታወቅ ነው። እኔ በቅርብ የማውቃቸውና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ ትልቅ የማምረት አቅም እያላቸው፤ ገበያ ላይ በጣም ተፈላጊ የሆነ ምርት ይዘው የተቀመጡ አሉ። እነዚህ ድርጅቶች ከፍተኛ የሆነ የማምረት አቅም እያላቸው ነገር ግን 10% እና 15% የማምረት አቅማቸውን ብቻ እየተጠቀሙ ካፒታላቸውን አስረው የተቀመጡ ኢንቨስተሮች በርካቶች ናቸው። ታዲያ እነዚህ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሬን በሰፊው ማግኘት ሲጀምሩ ምርታማ የመሆን ዕድላቸውና ተወዳዳሪ የመሆን አቅማቸው ይጨምራል። በሙሉ አቅማቸውም ማምረት ሲጀምሩ ለበርካቶች የስራ ዕድልንም የሚፈጥሩ ይሆናል ማለት ነው። ይህ እንግዲህ የስቶክ ማርኬት በግለሰቦች፣ በማህበረሰብ፣ እንዲሁም በጥቅል የአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነው የሚያሳየን።

   እንግዲህ ስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ በሚጀምርበት ጊዜ እያንዳንዳችን ምን ዓይነት ሚና መጫወት እንደሚጠበቅብን ባለሙያዎች እንደ ባለሙያ፤ ኢንቨስተሮች እንደ ኢንቨስተር፤ ኩባንያዎች እንደ ኩባንያ እንዲሁም መንግስት እንደ መንግስት የተለያዩ ዕድሎችን ለመጠቀም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ማለት ነው።

❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤