በዛሬው ፕሮግራማችን የምንመለከተው በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ ውጤታማ ሊያደርጉን ስለሚችሉ አስደናቂ ስትራቴጂዎች ይሆናል።

    እንግዲህ የዘርፉ ምሁራን በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ ውጤታማ ሊያደርገን የሚችለውን ይህን አስደናቂ ስትራቴጂ በቀላሉ ልናስታውሰው በምንችለው መልኩ አስቀምጠውታል። ይህም ውጤታማ ስትራቴጂ በአማርኛው "ብርርርር" ሲባል በኢንቨስትመንት ቋንቋ ደግሞ "BRRRR" እየተባለ ይጠራል። በእርግጥም ይህ ስያሜ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከምንጠቀመው የገንዘብ ኖት ስያሜ ጋር ቢመሳሳልም የዚህ ድምፀት ግን ትንሽ ዘለግ ያለ ነው።

ይህ ብርርርር የተሰኘው የሪልስቴት ኢንቨስትመንት ሁነኛ ስትራቴጂ ምን ማለት ነው? የሚለውን በምናይበት ጊዜ ብርርርር የሚለው ቃል BRRRR ከሚለዉ የእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃል በቀጥታ የተወሰደ ነው። እንግዲህ ማናችንም በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ ስንፈልግ ብርርርር የሚለውን ስትራቴጂ ማስታወስ ያስፈልጋል ማለት ነው። የዚህን ውጤታማ ስትራቴጂ ትርጓሜ ወይም ትንታኔውን በምናይበት ጊዜ፦

     1. B - Buy (መግዛት)

     2. R - Rehabilitation (ማደስ)

     3. R - Rent (ማከራየት)

     4. R - Refinance (መበደር ወይም መሸጥ)

     5. R - Repeat (መድገም - BRRRR)

ስለዚህ BRRRR የሚለው ምህፃረ ቃል ሲተነተን ከላይ ያየነውን ይመስላል ማለት ነወ። እንግዲህ በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ውስጥ ውጤታማ ለመሆን የምንከተላቸው እነዚህን መንገዶች ነው ማለት ነው። በዚህ ስትራቴጂ መሰረት በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ላይ ቤት፣ አፓርታማ፣ መሬት፣ ሱቅ ወዘተ. ላይ ኢንቨስት ስናደርግ የመጀመሪያው ነገር መግዛት (Buy) ነው። ምክንያቱም ያንን ነገር እስካልገዛነው ድረስ በሪልስቴት ላይ ኢንቨስት አድርገናል ማለት አይቻልምና ነው። በዚህም መሰረት ለምሳሌ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈን ቪላ ቤት ከነ ሙሉ ግቢው አሁን ላይ ባለው የቤት ገበያ በ20 ሚሊዮን ብር ገዛነው እንበል፤ በዚህም መግዛት የሚለውን ስትራቴጂ ተገበርን ማለት ነው። ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ማደስ (Rehabilitation) የሚለው ነው። በ20 ሚሊዮን ብር የገዛነው ይህ ቪላ ከዚህ ቀደም የተኖረበት ቤት በመሆኑ እኛ በምንፈልገው መልኩ ለምሳሌ የቤቱን ቀለም መቀየር፤ የተጓደሉ ነገሮችን ማሟላት፤ የውስጡን ዲዛይን በአዲስ መልክ መቀየር፤ የውስጥ ዕቃዎቹን በአዲስ መልክ ፈርኒሽ ማድረግም ሊሆን ይችላል። ለዚህ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር ወጭ ብናደርግ በአጠቃላይ በቤቱ ላይ 21 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት አደረግን ማለት ነው። ቤቱን አደስነው ማለት ደግሞ ዋጋውን ከፍ እያደረግነው ነው ማለት ነው። ለምሳሌ የዚህ ቤት እድሳት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ቢጠናቀቅና በዚህ ወቅት ቤቱን እንሽጠው ብንል እንኳ በእርግጠኝነት ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ሊያወጣ ይችላል። መሸጥ ብቻም ሳይሆን ይህን ቪላ በባንክ አሲዘን ልንበደርበት ብናስብ እንኳ ቤቱ ከ 25 - 27 ሚሊዮን ብር ድረስ ሊገመት ይችላል። ምክንያቱም ቤቱን በዘመናዊ መልኩ አድሰነዋልና። ይህን ሁሉ የምናገኘው ደግሞ ሁለተኛውን ስትራቴጂ (Rehabilitation) በመተግበር ብቻ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ማለት ነው።

    ከዚህ በመቀጠል የምናገኘው ደግሞ ማከራየት (Renting) የሚለውን ስትራቴጂ ነው። ይህም ማለት ቤቱን አድሰን ከጨረስን በኋላ ገቢ እንዲያመጣ ማድረግ መቻል አለብን። ከእነዚህ ገቢ አምጭዎች አንዱ የሆነው ደግሞ ቤቱን ማከራየት ነው። ለምሳሌ ይህ ቤት ከመታደሱ በፊት 30 ሺህ ብር ይከራይ ከነበረ፤ ከታደሰ በኋላ ደግሞ በ35 ሺህ ብር ልናከራየው እንችላለን ማለት ነው። አንዳንዶች የቤቱ የመሸጫ ዋጋ እስኪጨምርላቸው ድረስ ቤቱን ሳያከራዩ እንዲሁ አስቀምጠው የሚጠብቁ አሉ። ይህ ደግሞ ትክክለኛ አካሔድ አይደለም። ምክንያቱም ይህ ኢንቨስትመንት እስከሆነ ድረስ ቤቱ እስኪሸጥ ድረስ በማከራየት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ይቻላልና ነው። ከዚህ አኳያ በወር 35 ሺህ ብር የተከራየ ቤት በዓመት፣ በሁለት አሊያም በሦስት ዓመት ውስጥ ምን ያህል ገቢ ያስገኛል? የሚለውን እንኳ ብናሰላው በጣም ትልቅ ገንዘብ ነው። ስለዚህ በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ውስጥ ማከራየት (Renting) አንደኛው ገቢ አምጪ ስትራቴጂ መሆኑን ልብ ይሏል።

    አራተኛው ስትራቴጂ ደግሞ መበደር (Refinancing) የሚለው ነው። በዚህ ስትራቴጂ ውስጥ ሁለት ዓይነት ነገሮችን የምናገኝ ሲሆን እነዚህም በመደር ወይም መሸጥ የሚሉት ናቸው። በዚህም መበደር የሚለውን ስናይ ቤቱ ተከራይቶ ሳለ በባንክ አሲይዘን ልንበደርበት እንችላለን ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ከታደሰ በኋላ 25 ሚሊዮን ብር ቢያወጣና የዋጋውን 80% ማለትም 20 ሚሊዮን ብር ብንበደርበት ሁለት ዓይነት ገቢ አገኘን ማለት ነው። ይኸውም አንደኛው ገቢ ከኪራይ የምናገኘው ሲሆን ሁለተኛው ገቢያችን ደግሞ ከባንክ ተበድረን ያገኘነው 20 ሚሊዮን ብር ናቸው። እነዚህን ገቢዎቻችንን ይዘን ወደ አምስተኛውና መድገም (Repeat) ወደሚለው ስትራቴጂ እናመራለን ማለት ነው። ይኸውም ምንድነው ከኪራይ በወር 35 ሺህ ብር (በዓመት ሲሰላ ደግሞ 470 ሺህ ብር) እና ከባንክ በብድር መልክ ካገኘነው 20 ሚሊዮን ብር ጋር በአጠቃላይ 20,470,000.00 ብር ስለሚኖረን ይህንን ገንዘብ በመያዝ ሌላ ቤት መግዛትና ከላይ ያየናቸውን ስትራቴጂዎች በአዲሱም ቤት ላይ መድገም ነው። በዚህም መሰረት ቤቱን እናድሰዋለን ማለት ነው። ስናድስም እኛ እንደምንፈልገውና ቤቱ እንደሚያስፈልገው መጠን ገንዘብ ወጪ ልናደርግ እንችላለን። ከዚህ በመቀጠል የሚመጣው ደግሞ ቤቱን ማከራየት ነው ሲሆን በአራተኛ ደረጃ የምናገኘው ደግሞ ቤቱን አሲይዘን እንበደርበታለን ነው።

    ከዚህ እንደምንረዳው መጀመሪያ ላይ በ20 ሚሊዮን ብር ከገዛነው ቤት ከእድሳት በኋላ ዋጋው ወደ 25 ሚሊዮን ብር በማሻቀቡ 5 ሚሊዮን ብር አትርፈንበታል ማለት ነው። ሁለተኛ ከገዛነው ቤት ደግሞ በ20,470,000.00 ብር ገዝተነው በ25 ሚሊዮን ብር ብንሸጠው ወደ 4 ሚሊዮን ብር ስናገኝ፤ በአጠቃላይ የኪራዩ ተጨምሮበት ወደ 10 ሚሊዮን ብር ገደማ አገኘን ማለት ነው። ይህ የሚያሳየው የሪልስቴት ኢንቨስትመንት ምን ያህል አዋጪና አትራፊ እንደሆነ በዚች አጭር ገለፃ ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ ተስፋ አደርጋለሁ!!


❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤