ስቶክ ማርኬት ወይም በሌላ ስያሜው ካፒታል ማርኬት የሚባለው ይህ አዲስ ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ብዙዎችም በዚህ አዲስ ኢንዱስትሪ ላይ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ በኩባንያ ደረጃ፤ በትልልቅ ሼር ካምፓኒ ደረጃ  የተቋቋሙ ድርጅቶች ነጋዴዎችና በተለያዩ የስራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት እየተዘጋጁ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። የኢትዮጵያ መንግስት የካፒታል ማርኬትን ለማቋቋምና ለመምራት የሚያስችለውን የህግ የህግ ማዕቀፍ በረቂቅ ደረጃ አዘጋጅቶ የጨረሰ ሲሆን በቀጣይ የሚጠበቀው ደግሞ በሚመለከተው አካል ፀድቆ ወደ ስራ የሚገባበት ደረጃ ነው ያለው።

   ብዙዎች የስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ መከፈት ለህዝቡ የሚያመጣው ጠቀሜታ ምንድነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። እኔም የስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ መጀመሩ ስላለው ፋይዳ በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ።

   እንግዲህ ካፒታል ማርኬት በአብዛኛው የሚሰራው ገንዘብን ከአንድ ቡድን ወደ ሌላ ቡድን እንዲሸጋገር የማድረግና የማሳለጥ ስራን የሚሰራ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው። ይህን ገንዘብን የማስተላለፍና የማሰራጨት ስራ በዋናነት እየሰሩ ያሉት ባንኮች ናቸው። እንደሚታወቀው ባንኮች ከደንበኞቻቸው የተቀበሉትን ተቀማጭ ገንዘብ በብድር መልክ ወደ ሌላ ግለሰብ ወይም ተቋም ያስተላልፋሉ። በመሆኑም ባንኮች የፋይናንስ ስርጭትን በማሳለጥ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። በቢዝነስ ቋንቋ "ዲፖዚተሪ ኢንተርሚዲዬሪ ኢንስቲቲዩሽን" እየተባሉ ይጠራሉ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ገንዘብን ለጊዜው ከማይፈልገው አካል ወደሚፈልገው አካል የሚያስተላልፍና የሚያቀላጥፍ ሌላኛው ተቋም ደግሞ የካፒታል ማርኬት ሲስተም (capital market intermediary system) በመባል የሚታወቀው ነው። ይህም እንግዲህ የተለያዩ የገንዘብ ሰነዶችን ማለትም ስቶኮችን፣ ቦንዶችን እንዲሁም ከስቶኮች የሚወጡ "ዴሪቬቲቭስ" የሚባሉ የመገበያያ ሰነዶችን ከኢንቨስተሮች ወደ ኩባንያዎች፤ ከኢንቨስተሮች ወደ መንግስት ተቋማት በማሸጋገር መንግስትም የበለጠ ካፒታል አግኝቶ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያነት እንዲያውለው ያደርጋል። የግል ተቋማትም እንደገና ደግሞ ራሳቸውን ለማሻሻል፤ የማስፋፊያ ስራዎችን ለመስራት፤ የአጭር ጊዜም ሆነ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ፍላጎቶችን ለሟሟላት የሚያስችላቸውን ካፒታል እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ይህም በአገራችን በቅርቡ በስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

   የዓለምን ተሞክሮ በምንመለከትበት ጊዜ በአሁኑ ወቅት የዓለም ኢኮኖሚ አጠቃላይ የGDP ድምር 87.75 ትሪሊዮን ዶላር ያህል እንደሆነ ይታመናል። እንግዲህ ከዚህ አንፃር ሲታይ በስቶክ ማርኬት ላይ ያለው አጠቃላይ ዋጋ ሲደመር 87.83 ትሪሊዮን ዶላር ያህል እንደሆነ ይገመታል። ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ስቶክ ማርኬት ምን ያህል የዓለምን አጠቃላይ GDP እንደሚበልጥ ነው። በዚህም የተነሳ ስቶክ ማርኬት ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታር መህኑንና በዓለም ላይ ያለውን ከፍተኛ ተፈላጊነት መገንዘብ እንችላለን ማለት ነው። በተለይ እንደ አሜሪካና አውሮፓ ያሉ አገራት (ጃፓንን ጨምሮ) በምንመለከትበት ጊዜ ስቶክ ማርኬት የገንዘብ ስርጭት ተቋማት ከሆኑት ከባንኮች በላይ እጅግ በጣም ተመራጩ የገንዘብ አስተላላፊ ሲስተም ነው። እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ባሉ አገራት ደግሞ እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ተደርጎ ይታያል።

  ስለ ስቶክ ማርኬት ወይም ካፒታል ማርኬት ይሄን ያህል ካልኩኝ ዘንዳ ሰዎች ስለዚህ የገበያ ሲስተም በቅጡ ካለማወቅ ወይም ካለመረዳት የተነሳ ብዙ የተሳሳቱ አስተያየቶችን ሲሰጡ የሰማሁባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። እንደውም በቅርቡ ለስራ ጉዳይ ወደ ሜክሲኮ አካባቢ ጎራ ባልኩበት አጋጣሚ ከአንድ የንግድ ህንፃ ስር በትልቅ ባነር ላይ ስቶክ ማርኬት የሚል ፅሁፍ ተሰቅሎ አየሁ። እኔም በቃ መንግስት የስቶክ ማርኬት ቢሮውን እዚህ ከፈተ ማለት ነው? ብዬ መኪናዬን ወደኋላ መልሼና ባነሩ ወደተረሰቀለበት ህንፃ ጠጋ ብዬ ስመለከት ባነሩ ያለበት ቦታ የህንፃው ክፍል ውስጥ የሚሸጠው ጫማና የተለያዩ አልባሳት ነበር። እንግዲህ ይህ ባነር የሱቁ መለያ ስም መሆኑ ነው። ይህ የሚያሳየው ስለ ስቶክ ማርኬት ያለን ግንዛቤ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የስቶክ ማርኬትን መከፈት በእጅጉ እንደሚፈልጉት የሚናገሩ አንዳንድ ነጋዴዎችም እንዲሁ አጋጥመውኛል። እኔም የስቶክ ማርኬቱን መከፈት ለምን እንደሚፈልጉት ስጠይቃቸው አንደኛው የመለሰልኝ መልስ ትንሽ ፈገግ ያሰኝ ነበር። ሰውዬው ምክንያቱን ሲነግረኝ "እኔ ከቻይና፣ ከዱባይና ከታይላንድ የተለያዩ ሸቀጦችንና አልባሳትን ገዝቼ በመጋዘኔ ውስጥ አስቀምጫለሁ። ስለዚህ የስቶክ ማርኬት ሲከፈት በጥሩ ዋጋ ለመቸብቸብ ጓጉቻለሁ።" ነበር ያለኝ። ይህ ሰው እንግዲህ ስለስቶክ ማርኬት ያለው ግንዛቤ ምንም እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ምክንያቱም ይህ ሰው ያከማቻቸውን ሸቀጦቹንና አልባሳቶቹን ስቶክ ማርኬት(በእሱ አረዳድ ግዙፍ የገበያ ማዕከል) ሲከፈት በእዚያ ለመሸጥ ማሰቡ ነው። ለዚህም ነው አገራችን የስቶክ ግብይትን ለመክፈት መዘጋጀቷ እንዳለ ሆኖ ከዚህ ጎን ለጎን ስለስቶክ ማርኬት በቂ የሆነ ግንዛቤ ለህብረተሰቡ መስጠት ያስፈልጋል። የዚህም ፕሮግራም መዘጋጀት ዋነኛ አላማም ይኸው ነው።

  እንግዲህ ስቶክ ማርኬት ስለሚያመጣው ጠቀሜታ ማየት ስንጀምር ስቶክ ማርኬትን በዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት የሚጠቀሙ አገሮች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዋናነት የሚያነሱት ጉዳይ የገንዘብ ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል የሚል ነው። የገንዘብ ምርታማነት ሲባል በውስን ሀብት ብዙ ሀብት ማምረት ማለት ነው። ለምሳሌ በግብርናው ዘርፍ አንድ አርሶአደር በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 500 ኩንታል ጤፍ ቢያመርትና ሌላኛው አርሶአደር ደግሞ በተመሳሳይ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 1000 ኩንታል ጤፍ ቢያመርት እነዚህ ሁለት አርሶአደሮች በተመሳሳይ የመሬት መጠን ላይ የተለያዩ ውጤቶችን አግኝተውበታል ማለት ነው። እንግዲህ ምርታማነትን ከመለካት አንፃር የተለያዩ የምርታማነት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ለምሳሌ የሰው ሃይል ምርታማነት፤ የማሽን ምርታማነት እንዲሁም የገንዘብ ምርታማነትን ማንሳት እንችላለን። ከእነዚህ መካከል የገንዘብ ምርታማነትን በምንመለከትበት ጊዜ ለምሳሌ አንድ ብር ኢንቨስት ሲደረግ ምን ያህል ብር ያስገኛል? የሚለውን ነው። አንዳንዶች በ30% የወለድ ምጣኔ (return rate) የምናገኝበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ካለና እንደገና ደግሞ በሌላ ቦታ በተመሳሳይ አንድ ብር በ10% "ሪተርን ሬት" ኢንቨስት ተደርጎ ከሆነ ያለው በሁለቱ መካከል ከፍተኛ የምርታማነት ልዩነት የሚኖር ሲሆን ከፍተኛውን የካፒታል ምርታማነት የሚያስገኘው በ30% "ሪተርን ሬት" ኢንቨስት የተደረገው ነው የሚሆነው። ስለዚህ ወደ ስቶክ ማርኬት በምንመጣበት ጊዜ የካፒታል ምርታማነት በአገር ደረጃ ያድጋል ማለት ነው። ይህ እንደምን ሊሆን ይችላል? የሚለውን በምናይበት ጊዜ ስቶክ ማርኬት (ካፒታል ማርኬት) የአንድ አገር የኢኮኖሚ ቴርሞሜትር በመባል ነው የሚገለፀው። እንደሚታወቀው ቴርሞሜትር የሙቀትን ከፍና ዝቅ ማለት የምንለካበት መሳሪያ እንደሆነ ሁሉ ስቶክ ማርኬም የአንድን አገር የኢኮኖሚ ሙቀት መለካት ይችላል እንደ ማለት ነው። ይህም ማለት ኢኮኖሚው ተሟሙቋል ወይስ ተቀዛቅዟል፤ የትኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው? የትኛው የንግድ ዘርፍ ነው? የትኛው ኩባንያስ ነው? የሞቀ ገበያ ወይም የተቀዛቀዘ ገበያ ያለው? የሚለውን ነገር ይለካል ወይም ይጠቁማል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ዘንዳ ስቶክ ማርኬት ይህንን የሚለካው እንዴትና በምንድነው? የሚለውን ስናይ በስቶክ ግብይት ውስጥ የስቶክ ዋጋ (stock price) እና "ስቶክ ኢንዴክስ" የሚባሉ ፓራሜትሮች ያሉ ሲሆን እነዚህ ደግሞ በየሰዓቱ፣ በየቀኑ፣ በየሳምንቱ ያለውንና የስቶክ ዋጋ የሚጠቁሙ ናቸው። የአንድ የንግድ ዘርፍ ወይም ኩባንያ አማካይ የስቶክ መጠን ከፍና ዝቅ ማለት በእነዚህ ፓራሜትሮች ጠቋሚነት ወዲያው ነው የሚታወቀው ማለት ነው። የአንድ ኩባንያ የስቶክ ዋጋው ከፍ አለ ማለት ኢንቨስተሮች በዚህ ኩባንያ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል ማለት ነው። ከፍ ያለ ፍላጎት ከፍ ያለ ዋጋ ያመጣል፤ ከፍ ያለ ዋጋ ደግሞ ከፍ ያለ ፍላጎት የሚያመጣ ይሆናል። ይህም ማለት ይህ ኩባንያ ከፍተኛ ትርፍ ያመጣል፤ ይህ ደግሞ ኢንቨስተሮች በኩባንያው ላይ የሚኖራቸውን ፍላጎት ይጨምራል፤ ኢንቨስተሮችን ሲያመጣ ደግሞ የዚያ ኩባንያ የስቶክ ዋጋ ወደላይ ያሻቅባል ማለት ነው። "የስቶክ ኢንዴክሶች" ደግሞ የስቶክ ዋጋዎችን በየሰዓቱ፣ በየቀኑ እንዲሁም በየሳምንቱ ያሳውቃሉ። ስለዚህ የአንድ ኩባንያ ወይም የንግድ ዘርፍ የስቶክ ዋጋው ከፍ አለ ማለት ኩባንያው ወይም የንግድ ዘርፉ አትራፊ ወይም አዋጭ ነው ማለት ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የስቶክ ዋጋቸው ዝቅ ያለባቸው የንግድ ዘርፎች ወይም ኩባንያዎች አዋጭነታቸው ወይም ትርፋማነታቸው የወረደ ነው ማለት ሲሆን በዚህ ጊዜ ደግሞ ተፈላጊነታቸው ይቀንሳል፤ ተፈላጊነታቸው ሲቀንስ ደግሞ የስቶክ ዋጋቸው እንዲሁ ይቀንሳል ማለት ነው። ለምሳሌ እኔ በየትኛው ኩባንያ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብኝ? ብዬ በማስብበት ጊዜ ወዲያውኑ የስቶክ ዋጋዎችን ማየት እጀምራለሁ። በዚህም ዝቅተኛ ወይም እየወረደ የመጣ የስቶክ ዋጋ ባለው ኩባንያ ላይ ኢንቨስት አላደርግም ማለት ነው። ምክንያቱም ገንዘቤን በዚህ ኩባንያ ላይ ኢንቨስት ባደርግ የማገኘው ትርፍ ዝቅተኛ መሆን ብቻም ሳይሆን ኢንቨስት ያደረኩትንም ላጣ ወይም ልከስር ስለምችል ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የስቶክ ዋጋው እያደገ ያለ ኩባንያ ወይም ኢንዱስትሪ ከሆነ ደግሞ በዚህ ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ይኖረኛል ማለት ነው። ምክንያቱም በእዚህ ኩባንያ ወይም ኢንዱስትሪ ላይ ኢንቨስት ባደርግ የማገኘው ትርፍ ከፍተኛ ስለሚሆን ነው። ይህንን ለማወቅ ደግሞ የስቶክ ዋጋ ጠቋሚዎች (stock indexes) የስቶኩን ዋጋ በየሰዓቱ፣ በየቀኑና በየሳምንቱ ስለሚያውቁ ከዚያ ተነስቼ ይሆናል ኢንቨስት የማደርገው ማለት ነው። ስለዚህ ኢንቨስት የማደርገው የስቶክ አሊያም የቦንድ ባለቤት ለመሆን ሳይሆን የተሻለ ትርፋማነት ባለው ኩባንያ ወይም ኢንዱስትሪ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የተሻለ ትርፍ ለማግኘት ነው። ስለዚህ ለየብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢንቨስተሮችም ጭምር በዚህ መልኩ ስለሚሔዱ አጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ያለውን ገንዘብ ወይም ካፒታል የበለጠ ትርፋማ ሊያደርጉ በሚችሉ ኢንዱስትሪዎች፣ ኩባንያዎች፣ ሴክተሮች ወይም ዘርፎች ላይ ኢንቨስት ይደረጋል። ስለዚህ ዝቅተኛ ካፒታልና ዝቅተኛ ትርፋማነት ካላቸው ኩባንያዎችና ኢንደስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ትርፋማነት ይሸጋገራሉ ማለት ነው። ምክንያቱም የስቶክ ዋጋቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ወይም እየወረዱ ካሉ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስተሮች ስቶካቸውን (አክሲዮናቸውን) ይሸጣሉ። ከዚህም ሽያጭ ያገኙትን ገንዘብ ወይም ካፒታል ከፍተኛ የስቶክ ዋጋ ባላቸውና ከፍተኛ ትርፋማነት ባላቸው ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት ያደርጉበታል ማለት ነው። ስለዚህ የስቶክ ማርኬት አደረጃጀት የስቶክ ዋጋዎችን በቀላሉ ማወቅ በሚያስችለን ሁኔታ በመሆኑ ገንዘባችንን የተሻለ አዋጭነት ባላቸው ኩባንያዎች አሊያም ኢንዱስትሪዎች ላይ ኢንቨስት እናደርጋለን ማለት ነው።

  ይህን እንግዲህ በአገራችን ካለው የኢንቨስትመንት ቀጠና አንፃር ስንመለከተው ብዙውን ጊዜ መረጃዎችን በወፍ በረር በመሰብሰብ ስለሆነ  ብዙዎቻችን ኢንቨስት የምናደርገው  የትኛው ኩባንያ ወይም ኢንዱስትሪ ወይም ሴክተር ትርፋማ እንደሆነ የምናውቅበት ሁኔታ ባለመኖሩ የተነሳ ኢንቨስት የምናደርገው የትርፋማነት ደረጃቸውን ሳናረጋግጥ ነው ማለት ነው። ስለዚህ የኢንቨስትመንት ሒደቱ የሚከተለው "Blind Investment " ያለበትን ቦታ ነው ማለት ነው የኢንቨስትመንቱ ቀጠና የሚከተለው። ይህም ማለትም የሆኑ ሰዎች በሆነ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ወይም ደግሞ በቱሪዝም፣ ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሆቴል ዘርፍ እንዲሁ ሾላ በደፈናው ኢንቨስት አድርገዋልና እኔም ከእነዚህ ዘርፎች በአንዱ ላይ ኢንቨስት ላድርግ ከማለት ውጭ ወደተሻለ ኢንቨስትመንት የሚመራን፤ በትክክለኛ የቁጥርና የስሌት ሪፖርት ላይ የተመሰረተ በቂ መረጃ የሚሰጠንና የሚመራን የተደራጀ ተቋም በአገራችን የለም። ስለዚህ የስቶክ ማርኬት በአገራችን መጀመር ለኢንቨስተሮች ትክክለኛውንና በጣም መሰረታዊ የሆነውን መረጃ በመስጠት የአንድን አገር ሀብት (resource) የተሻለና የበለጠ ውጤታማ በሆነ ኢንቨስትመንት ላይ ሀብታቸውን ፈሰስ ያደርጉ ዘንድ በማስቻል ዘርፈ ብዙ ሚና ይጫወታል ማለት ነው።

   ዝቅተኛ ተፈላጊነት ካላቸው ቦታዎች ላይ  ከፍተኛ ተፈላጊነት ወደአላቸውቦታዎች፤ ዝቅተኛ ውጤታማነት ወይም ምርታማነት ካላቸው ዘርፎች ወደ ከፍተኛ ውጤታማነት ወደአላቸው ኩባንያዎች እንዲፈስ በማድረግ ረገድ ዋነኛ የሙቀት መለኪያ መሳሪያ በመሆን ያገለግላል። በዚህ ረገድ እንግዲህ በስቶክ ማርኬት ከፍተኛውን የመሪነት ደረጃ የሚይዙት አሜሪካና እንግሊዝ ሲሆኑ በተለይ እንግሊዝ ከአውሮፓ አገራት በተሻለ  ኢኮኖሚዋ የሚመራው በዚህ በስቶክ ማርኬት ነው። እናም በእነዚህ አገራት ባለው የስቶክ ማርኬት ውጤታማነት ላይ በተጠናው ጥናት መሰረት በአሜሪካ 12% ሲሆን በእንግሊዝ ደግሞ 11% ነው። ስቶክ ማርኬት እንደ ሁለቱ አገራት ባልሆነባቸው ሌሎች አገራት ለምሳሌ በጃፓን የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው የስቶክ ማርኬት ምርታማነታቸው በአውሮፓ 12% ሲሆን በጃፓን ደግሞ 6% ነው። ይህም ማለት የካፒታል ማርኬት መር ኢኮኖሚ ያላቸው አገራት የተሻለ የኢኮኖሚ ቁመና እንዳላቸው ያሳያል ማለት ነው።

   ሌላው የምናነሳው ጉዳይ ስለትንንሽ አዳጊ ድርጅቶች ወይም ስለአዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ይሆናል። ይህም ሲባል ስቶክ ማርኬት ባላቸው አገራት ውስጥ አዳጊ ድርጅቶች ወይም አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ምን ያህል ቦታ አላቸው? ምን ያህል ገንዘብስ ያገኛሉ? በስቶክ ማርኬት "ኢኒሽያል ፐብሊክ ኦፈሪንግ" (IPO) ወስጥስ መመዝገብ ይችላሉ ወይ? ስቶክ ማርኬት ኢኮኖሚያቸውን በሚመራላቸው አገራት ውስጥስ የእነዚህ ድርጅቶች እጣፈንታ ምንድነው? የሚሉትን ጉዳዮች በዝርዝር እንመለከታለን ማለት ነው።

   በዚህ ረገድ የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ ድርጅቶች ገንዘብ ቢያገኙ የማደግ እድላቸው ሰፊ ስለመሆኑ እሙን ነው። ይህን የማደግ እድል የሚወስነው ደግሞ ገንዘብ የማግኘት እድላቸው ነው። ምክንያቱም እነዚህ አዳጊ ድርጅቶች ወይም አዳጊ ስራ ፈጠራዎች ገንዘብ በአገኙ ቁጥር አቅማቸውን የማሳደግ፤ ተወዳዳሪነታቸውን የማጎልበት አቅም ስለሚፈጥርላቸው የማምረት አቅማቸው ይጨምራል፤ ወደፊት ትልቅ ኩባንያ ወደመሆንም ይሸጋገራሉ ማለት ነው። ስለዚህ የካፒታል ፍሰትን በተመለከተ ስቶክ ማርኬት ባላቸው አገራት ላይም ከፍተኛ ካፒታል የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው ጥናቱ የሚያመላክተው። ይህ የሆነው ለምንድነው? በሚባልበት ጊዜ ስቶክ ማርኬት ባለበት አገር "ፕራይቬት ኢኩይቲ ወይም ቬንቸር ኢንቨስተርስ" የተሰኙ ተቋማት በእነዚህ አዳጊ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይበረታታሉ። የበለጠ የሚያበረታታቸው ነገር ደግሞ ስቶክ ማርኬት በመኖሩ የተነሳ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከዚህ ኢንቨስት ካደረጉበት ድርጀት መውጣት ሲፈልጉ ወይም ድርሻቸውን ሸጠው መውጣት ሲያሻቸው የሽያጭ ሒደቱ ድርሻቸውን በተሻለ ዋጋ ሸጠው እንዲወጡ እድሉን ስለሚፈጥርላቸው ነው። ነገር ግን ስቶክ ማርኬት በሌለባቸው አገራት ላይ "ፕራይቬት ኢኩይቲ ወይም ቬንቸር ካፒታል" የምንላቸው ተቋማት በአዳጊ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያበረታታቸው ወይም ደግሞ ወደፊት ድርሻቸውን ሸጠው ለመውጣት የሚያስችላቸውን ዕድል አያገኙም። ስለዚህ የስቶክ ማርኬት በአገራችን መከፈትን በጣም ልናበረታታውና በትኩረት ልንመለከተው የሚገባን ነገር ነው። በአገራችን ያሉ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን የስቶክ ማርኬት በአገራችን የመጀመርን ጉዳይ አስመልክቶ ፍፁም የተሳሳተና ያልተጠኑ አስተያየቶችን ሲሰጡ ይስተዋላል። ይኸውም ምንድነው "ስቶክ ማርኬት ወደ አገራችን ሲመጣ በሲስተሙ ውስጥ የሚመዘገቡ ድርጅቶች ብቻ ናቸው ገንዘብ ማግኘት የሚችሉት፤ ሌሎቹ አዳጊና አነስተኛ ድርጅቶች ወይም ደግሞ አትራፊነታቸው ያልተረጋገጡ ድርጅቶች በመሆናቸው የተነሳ ገንዘብ ማግኘት አይችሉም። ገንዘብ ካላገኙ ደግሞ በስቶክ ማርኬት ውስጥ መመዝገብ አይችሉም።" የሚል አመለካከት ነው ያላቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ስቶክ ማርኬት ላይ ለመመዝገብ የግድ አትራፊ ድርጅቶች መሆን አይጠበቅባቸውም። ከዚያ ይልቅ ወደፊት ሊያድጉ፤ ትርፋማ ሊሆኑ የሚችሉ (promising company) ከሆኑ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ከመመዝገብ የሚያግዳቸው ነገር ከቶውንም አይኖርም። ለምሳሌ "ቴስላ ሞተርስን" በምንመለከትበት ጊዜ ቴስላ ሞተር በአሜሪካን አገር በስቶክ ማርኬት አማካኝነት በፍጥነት ያደገ ካምፓኒ ነው። ይህ ካምፓኒ በ IPO (Initial Public Offering) ላይ ወዲያውኑ እንደተመዘገበ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፈላጊ የመጣበትና አሁንም ድረስ የስቶክ ዋጋው በየጊዜው እየተመነደገ ያለ ካምፓኒ ነው። ስለዚህ ቴስላ ሞተርስ በስቶክ ማርኬት ላይ ለመመዝገብ የግድ አትራፊ ወይም ግዙፍ ካምፓኒ መሆን አላስፈለገውም ነበር። ዋናው ነገር ምንድነው ድርጅቶቹ ያላቸው ወደፊት የማደግ ተስፋ ነው ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ማለት ነው። ስለዚህ እየተፈጠሩ ያሉ፤ ገና ትንንሽ የሆኑ፤ በማደግ ላይ ያሉ ወይም ደግሞ የማደግ ብሩህ ተስፋ ያላቸው ድርጅቶች በርግጥ ወዲያውኑ ላያተርፉ ይችሉ ይሆናል፤ እንዲያተርፉም አይጠበቅባቸውም። ነገር ግን ተፈላጊነታቸውን የሚጨምረው የሽያጭ ዕድገታቸው ነው። በዚህ ላይ ደግሞ የበለጠ እየተስፋፉ ስለሚሔዱና ወጪያቸውም እያደገ ስለሚሔድ ላያተርፉ ይችላሉ በመሆኑም እነዚህ ድርጅቶች አትራፊ መሆን ሳይጠበቅባቸው በስቶክ ማርኬት ላይ ተመዝግበው ገንዘብ የማግኘት እድል አላቸው ማለት ነው። በሁለተኛና በዋናነት ደግሞ እነዚህ ድርጀቶች ገንዘብ ለማግኘት ስቶክ ማርኬት ላይ መመዝገብ አይጠበቅባቸውም። እዚህ ላይ የሚፈልገው ነገር "ፕራይቬት ኢኩይቲና ቬንቸር ካፒታል ፈርም" የተሰኙ ተቋማትና ሌሎች ደግሞ አዳጊ ድርጅቶች ሆነው ነገር ግን ሪስክ የሚወስዱ ተቋማት አሉ። ስለዚህ ትንንሽ ድርጅቶች ለማደግ የሚያስችላቸውን ካፒታል ሄጅ ፈንድ በሚባሉ ተቋማት አማካኝነት ስቶክ ማርኬት ሲመጣ ይቋቋማሉ ማለት ነው። ስለዚህ ትንንሽ ወይም አዳጊ ድርጅቶች በስቶክ ማርኬት ላይ ለመመዝገብ የሚያድስላቸውን ካፒታል በዚህ መልኩ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው። ስቶክ ማርኬት ከሌለ ግን ወዲያውኑ ለመሸጥ የሚያስችላቸው ገበያ አይኖርም፤ እንደገና ደግሞ በሚፈልጉት ዋጋ ወይም በገበያው የዋጋ መጠን ገዢም ላያገኙ ይችላሉ። ስለዚህ የሊኩዲቲና የምርታማነት ጉዳይ ዝቅተኛ ይሆናል ማለት ነው። ይህም በመሆኑ የተነሳ ትንንሽ ወይም አዳጊ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ኢንቨስተሮች፣ ፕራይቬት ኢኩይቲ፣ ቬንቸር ካፒታል ፈርምና ሄጅ ፈንድ የመሳሰሉ ተቋማት አይኖሩንም ማለት ነው። በአገራችንም እንዲህ አይነቱ የፋይናንስ ሒደት በጣም ዝቅተኛ የሆነበት አንዱና ዋናው ምክንያት የስቶክ ማርኬት አለመኖር ነው። አሜሪካ ባለው የሲልከን ቫሊን ተሞክሮ በምናይበት ጊዜ ብዙ ስራ ፈጣሪዎች፤ ብዙ ፈጠራዎች እንዲበራከቱ ያደረጋቸው ትልቁ ምክንያት የፋይናንስ ቀጠናው ጤናማ በመሆኑ የተነሳ መነቃቃትን ስለሚፈጥርላቸው ነው። ስለዚህ በአሜሪካን አገር በርካታ ስራ ፈጣሪዎች ስኬታማ የመሆን እድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። የስራ ፈጠራ ባህሉም ደግሞ በጣም አነቃቂና ተስፋ ሰጭ ነው። ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የፋይናንስና የካፒታል አማራጮች በርካታ በመሆናቸው የተነሳ ነው። ስለዚህ በአገራችን የስቶክ ማርኬት መኖር ውጤታማ ስራ ፈጣሪዎች እንዲኖሩና የስራ ፈጠራ ባህሉም እንዲስፋፋ ያደርጋል ማለት ነው።

  በሦሥተኛና በዋናነት የምናገኘው ደግሞ ሪስክን (የመክሰር ዕድልን) በተመለከተ ይሆናል። በኢንቨስትመንት ውስጥ ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች አሉ። አንደኛው ትርፋማነት (ሪተርን) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመክሰር እድል (ሪስክ) ነው። ከላይ ለማየት እንደሞከርነው የካፒታል ማርኬት ምርታማነትን (ሪተርንን) የማሳደግ ዕድልን እንደሚሰጠን ሁሉ የአንድን ኢንቨስትመንት የመክሰር ዕድል ወይም ሪስክን በመቀነስ ረገድም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ምክንያቱም ሪስክን በአንድ በኩል መቆጣጠር ካልቻልን ምርታማነት ብቻውን የትም አያደርሰንም ማለት ነው። ምክንያቱም ሪስክ ማለት የኪሳራ ዕድል በመሆኑ ይህንን ከመቆጣጠር አንፃር ስቶክ ማርኬት ከፍተኛ ሚና ይጫወታልና ነው። ስቶክ ማርኬት ይህንን ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? የሚለውን ስናይ ቅድም ለማንሳት እንደሞከርኩት በአዳጊ ወይም በትንንሽ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሪስክ አለው። ምክንያቱም የእነዚህ ድርጅቶች ትርፋማነት ገና ያልተረጋገጠና የተፈተሸ ባለመሆኑና ትርፋማነታተው ሊረጋገጥ የሚችለው ገና ወደፊት በመሆኑ በእነዚህ ድርጅቶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የግድ ሪስክ መውሰድ ያስፈልጋል ማለት ነው። ይህንን ሪስክ እንድንወስድ የሚያደርገን ደግሞ የስቶክ ማርኬት መኖር ነው። ስቶክ ማርኬት በመኖሩ የተነሳ ወደፊት የተሻለ ትርፍ አገኝበታለሁ በሚል ድርሻውን ሸጦ ለመውጣት ፍላጎቱ ስለሚኖር ያንን ሪስክ ኸደ መውሰድ እናመራለን ማለት ነው። ነገር ግን ስቶክ ማርኬት ከሌለ ሪስክ ለመውሰድ የሚያደፋፍረኝ ምክንያት አይኖርም። ምክንያቱም ወደፊት ድርሻዬን ሸጬ አትርፌ የመውጣት ዕድሌ የጠበበ ነውና። ስለዚህ አንዱና ወሳኙ ነገር ሪስክን ለሚጋፈጡ ድርጅቶች እነዚህ አዳጊ ድርጅቶች ሪስካቸውን ለማስተላለፍ ስለሚያስችላቸው ነው።

  በስቶክ ማርኬት ሌላኛውና ወሰኙ ነገር ደግሞ በዚህ የግብይት ስርዓት ውስጥ ትልቅ የግብይት ዕድልን የሚፈጥሩልን ደሪቫቲቭስ የሚባለው ነገር ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የደሪቫቲቭስ ገበያ 187 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን ይህ ደግሞ ከስቶክ ማርኬት የግብይት ዋጋ በላይ ያደርገዋል። እነዚህ ደሪቫቲቭስ የምንላቸው ብዙውን ጊዜ ዋጋቸውን ከስቶክ የሚያገኙ፤ ስቶኮች ባሉ ቁጥር የእነሱም ዋጋና ግብይት ከእነሱ ሊነሳ የሚችል ገበያ ማለት ነው። ስቶክ ማርኬት በራሱ ሰፊ በመሆኑ በውስጡም ወርቆች፣ ቦንዶች፣ ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮችን ይዟል ማለት ነው። ስለዚህ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ያሉ ደሪቫቲቭስ ዋና ዋጋቸውንና የሽያጭ ሒደታቸውን የሚያገኙት ከዋናው ምርት በመሆኑ እነዚህ ደሪቫቲቭሶች የኢንቨስተሮችን የኪሳራ ዕድል ወይም ሪስክ ከመከላከል አኳያ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል። በተለይ ደግሞ ወደ ስቶክ ማርኬት በምንመጣበት ጊዜ "stock options" የምንላቸው ነገሮች አሉ። እነዚህንም በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን........ እና..........  በመባል ይታወቃሉ። እነዚህም ስቶኮችን ወይም አክሲዮኖችን ከገበያ ላይ በገዛን ቁጥር እንደ ኢንሹራንስ (ማለትም የገዛነው ስቶክ ቢከስርብን ስቶክ ኦብሽኖች የማካካሻ ዕድሎችን ይፈጥሩልናል ማለት ነው።) ስለዚህ ስቶክ ኦብሽኖች እንዲህ ዓይነቱን ሪስክ የመከላከል ዕድልን ስለሚሰጡ ኢንቨስትመንትን ያበረታታሉ ማለት ነው። ምክንያቱም ኢንቨስትመንት ሲበረታታ የኢንቨስትመንት ሪተርን ወይም ምርታማነት ያድጋል፤ እንደ አገር ደግሞ ኢኮኖሚውም በዛው ልክ ያድጋል ማለት ነው። ስለዚህ ስቶክ ማርኬት የኪሳራ ዕድልን ለመቀነስ የሚያስችል ሁኔታንም ይፈጥርልናል ማለት ነው። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ያልን እንደሆነ በስቶክ ማርኬት ላይ አንድ ትልቅ የኢንቨስትመንት መሳሪያ አለ። ይህም መሳሪያ ፖርትፎሊዮ ማኔጀመንት ይባላል። ይህም ማለት አንድ ኢንቨስተር በአንድ ወይም በሁለት ስቶኮች ላይ ብቻ ተማምኖ ኢንቨስት አያደርግም። ከዚያ ይልቅ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን መያዝ ይኖርበታል ማለት ነው። ምክንያቱም አንደኛው ኢንቨስትመንት ሲወርድበት ወይም ሲከስርበት ከሌላኛው ኢንቨስትመንት ትርፍ ማግኘት የሚያስችለው እንዲሆን ነው። ምክንያቱም ያለውን ገንዘብ በሙሉ አሟጦ በአንድ ወይም በሁለት ኢንቨስትመንት ላይ ብቻ ኢንቨስት ቢያደርግ ኢንቨስት ያደረገበት ስቶክ ዋጋው ቢወርድ ገንዘቡን ሊያጣ ወይም ደግሞ ሊያገኝ ይችል የነበረው ትርፍ ሊቀንስ ይችላልና። በስቶክ ማርኬት ላይ በርካታ ስቶኮችን መያዝ የሚያስችል ህግም ስላለ በርካታ ስቶኮችን መያዝ ይመከራል ማለት ነው። ይህን ደግሞ የዳይቨርስፊኬሽን ህግ እንለዋለን። ይህንን ህግ ተግባራዊ ማድረጉ የሚጠቅሙው ዝቅ ያለ የኪሳራ ዕድል ወይም ሪስክ ያላቸውን ስቶኮችንና ከፍተኛ የመክሰር ዕድል ያላቸውን ስቶኮች በአንድ ላይ ለመያዝና ለመቆጣጠር ያስችለናል ማለት ነው። ስለዚህ ከፍ ያለ ሪስክ ያላቸው ኢንቨስትመንቶችም በሌሎች ዝቅተኛ ሪስክ ባላቸው ኢንቨስትመንቶች የምንይዛቸው በመሆኑ ከፍተኛ ሪስክ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች ኢንቨስት ሳይደረግባቸው አይቀሩም ማለት ነው።በዚህም የተነሳ አንዱን ሪስክ በሌላኛው እንድንከላከል የሚያስችለን የፖርትፎሊዮ ማኔጅመንትን ስቶክ ማርኬት የሚያመጣልን በመሆኑ በዚህ መንገድ የኪሳራ ዕድልን ወይም ሪስክን እንቀንሳለን ማለት ነው። አሊያም ደግሞ ከዚህ ቀደም በአንድ ኢንቨስትመንት ላይ ብቻ ኢንቨስት በማድረጋችን ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶብን ሊሆን ይችላል ነገር ግን ስቶክ ማርኬት ይህንን ኪሳራ የመከላከል ዕድል ያመጣልናል ማለት ነው። በሌላ አገላለፅ የኪሳራ መከላከያ ጋሻን ይሰጠናል ማለት ነው።

❤❤❤❤❤❤❤❤❤❤